ጥንዶቹ በሰርጋቸው እለት ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደም ለገሱ

63

በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ ላይ ጋብቻቸውን እየፈፀሙ የነበሩ ጥንዶች ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ አደረጉ።

የአቶ አየነው ሞገስ እና የወይዘሪት ሩት ወርቁ በጋብቻ ስነ ስርአታቸውን ዕለት ህዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም ሲካሄድ ለሰራዊቱ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ደም ለግሰዋል።

ሰሞኑን በሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ዘራፊው የህወሀት ጁንታ ቡድን የፈጸመው አስነዋሪ ተግባር በጥንዶቹ ላይ ያሳደረው ቁጭትና እልህ ነፍጥ አንግበው ጦር ሜዳ ሄዶ መፋለም ባያስችላቸውም በደስታቸው እለት ደም በመለገስ ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡

"የሀገር ጉዳይ ከምንም በላይ ነው" ያሉት ጥንዶቹ፤ በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ ለሠርጋቸው በታደመው ህዝብ ፊት ደም በመለገስ የህይወታቸውን ጣፋጭ ጊዜ በበጎ ተግባር አሀዱ ብለው ጀምረዋል፡፡

ሀገርን ክዶ የገዛ ወገኑ ላይ ብረት አንስቶ እየተዋጋ ያለውን ወንበዴ ቡድን አደብ ለማስገዛት በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ሀገር እያቀና ላለ ጀግና በደስታ ቀን ደም መለገስ ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም ሲሉ ነው ጥንዶቹ የተናገሩት፡፡

ሙሽሮቹን ተከትለው ሚዜዎቹም ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ደም ለመለገስ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሰርጉ ታዳሚዎች እንዲህ አይነቱ ጥልቅ የሀገር ስሜት ለበርካቶች በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡

ምንጭ፡- የደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም