ቀጣዩ የከተማ አስተዳደሩ ዋና የስራ ትኩረት የመልካም አስተዳደር ችግርን መፍታት መሆን አለበት - አምባሳደር ድሪባ

97
አዲስ አበባ  ሀምሌ 10/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀጣይ ዋና የስራ ትኩረት የመልካም አስተዳደር ችግርን መፍታት መሆን እንዳለበት የቀድሞው ከንቲባ አምባሳደር ድሪባ ኩማ ገለፁ። ከንቲባው በዛሬው እለት እርሳቸውን ለሚተካ ሹመኛ ስልጣናቸውን ያስረከቡ ሲሆን ባለፉት አምስት አመታት የሰሯቸውን ስራዎችና ተግዳሮቶችን በተመለከተ ከአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ከንቲባው ከኤጀንሲው ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ ባለፉት አምስት አመታት በከተማዋ በተከናወኑ የተለያዩ ስራዎች አንፃራዊ ለውጥ መጥቷል። በተለይም በመሬት አሰጣጥና ግንባታ ዙሪያ በርካታ ችግሮች እንደነበሩና ጠንካራ አሰራር እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። ይህንንም ለመፍታት ከመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ጋር የተያያዙ ዘመናዊ አሰራሮችን በመጠቀም ችግሩን ለመቀነስ ጥረት መደረጉንም ገልፀዋል። በመሆኑም በመልካም አስተዳደር ላይ የተጀመረውን ትግል በማጠናከርና እየመጣ ያለውን ለውጥ አጠናክሮ በመሄድ መልካም አስተዳደርን ማስፈን የከተማ አስተዳደሩ ቀጣይ ትልቁ ትኩረት መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል። ለዚህም ለህዝብ ክፍት የሆኑ፣ ግልፅ አሰራር ያላቸው ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባትና ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል። የቀድሞው ከንቲባ አያይዘውም ከቤቶች ግንባታና ተደራሽነት አኳያ ብዙ ችግሮች ቢያጋጥሙም ለነዋሪዎች በእጣና በኪራይ ቤቶችን በማከፋፈል የቤት ችግሩን ለማቃለል መሞከሩን ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት የተለቀቁ የቀበሌ ቤቶችን በማስተላለፍ የነዋሪውን የቤት ችግር ለማቃለል ጥረት መደረጉን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም በርካታ ቤቶች ግንባታ ላይ መሆናቸውንና የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ላለፉት ጊዜያት አጋጥሞ የነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት የጥራትና የግንባታ መጓተት ማስከተሉን አስታውሰው የአስተዳደሩ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንዲሆንም አመላክተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም