ችግኝ በመትከል በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ጀምረናል - የጣርማ በር ወረዳ አርሶ አደሮች

74
ደበረ በርሃን ሀምሌ 10/2010 በተለያየ ምክንያት በተራቆተ ማሳቸው ላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ችግኝ በመትከል ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን በሰሜን ሸዋ ዞን የጣርማ በር ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ "የደን መመናመንና መመንጠርን በመከላከል የአየር ንብረት ለውጥን እንከላከል " በሚል መሪ ቃል   የዞኑ የችግኝ ተካላ መርሃ ግብር በጣርማ በር ወረዳ  ተጀምሯል፡፡ በዚሁ ወቅት አርሶ አደር  ቄስ ለማ ተስበ ለኢዜአ እንደገለጡት  ባለፉት ዓመታት የተካሄደው የችግኝ ተከላ ተራቁቶ የነበረውን አካባቢ ልምላሜ ወደነበረበት ከመመለስ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል፡፡ በአፈር ለምነት መታጣት ምክንያት ከሰብል ምርት ውጪ በሆነ  አንድ ጥማድ መሬታቸው ላይ ባለፉት ዓመታት የተከሉትን የባህርዛፍ  ተክል ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡ ይኸው ተጠቃሚነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም በተያዘው የክረምት ወቅት 10 ሺህ የባህር ዛፍ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት  በአሲዳማነት ተጠቅቶ  ከምርት ውጪ የነበረ ሁለት ጥማድ መሬታቸውን በባህርዛፍ ተክል በመሸፈን እየተንከባከቡ መሆኑን የገለፁት ደግሞ አርሶ አደር ተክልየ ይርጉ ናቸው ፡፡ ከእርሻ መሬታቸው ያጡት የሰብል ምርት በደን ልማት እንደሚካካስላቸው ተስፋ የሰነቁት አርሶ አደሩ ለሚተክሉት ችግኝ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ሰፈፍየለሽ እሸቴ በበኩላቸው ከምርት ውጪ የሆነ  መሬታቸውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለው ችግኝ በመሸፈን በሚያገኙት ገቢ  ቤተሰባቸውን ማስተዳደራቸውን ገልፀዋል፡፡ በዞኑ ግብርና  መምሪያ  የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጌታነህ ተክለማሪያም  እንደገለጡት  በተያዘው የክረምት ወቅት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው 297 ሚሊዮን ችግኝ በመተከል ላይ ነው፡፡ ችግኙ በመተከል ላይ ያለው በ950 ተፋሰሶች በሚገኝ   35 ሺህ 355 ሄክታር መሬት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አርሶ አደሩ በደን ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ያለው ግንዛቤ ማደጉ  የችግኙ መጽደቅ መጠን አሁን ካለበት 75 ከመቶ ወደ 83 ከመቶ ለማድረስ መታቀዱን ጠቁመዋል ፡፡ የዞኑ የደን ሽፋን አሁን 15 ከመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን በመተከል ላይ ያለው ችግኝ ሽፋኑን ወደ  16 ነጥብ 9 ከመቶ ያሳድገዋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም