15 የመንግስት ተቋማት የተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂውን አልተገበሩም - ኮሚሽኑ

203
ግንቦት 5/2010 የተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂውን 15 የመንግሥት ተቋማት ተግባራዊ አለማድረጋቸውን የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ። የኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንዳሉት እስካሁን በተደረገው ክትትል 50 ያህል ተቋማት በተሻለ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ አብዛኞቹ ተቋማት መካከለኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን 15 የመንግሥት ተቋማት ግን ስትራቴጂውን ተግባራዊ አለማድረጋቸውን ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት፡፡ በስትራቴጂው አተገባበር የተሻሉ ተቋማት ሙስናን የመከላከል ስራውን በሃላፊነት ስሜት ለመስራት ስልቶችን ነድፈው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ያብራሩት ዳይሬክተሩ ስራዎቻቸውንም በየጊዜው ለኮሚሽኑ በሪፖርት እያሳወቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት አንዳንድ ተቋማት የሙስና መከላከል ስራውን የኮሚሽኑ ብቻ አድርገው በመውሰዳቸው ስትራቴጂውን እስካሁን አልተገበሩትም፡፡ የስነ ምግባር መከታተያ ክፍል የሌላቸው ተቋማት መኖራቸውን ያብራሩት ዳይሬክተሩ ያሉትም በአግባቡ አለመደራጀታቸው ስትራቴጂው እንዳይተገበር ማድረጉን ነው ያብራሩት፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን በተቋማት የተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ዝግጅትና አተገባበር የተሻለ አፈፃፀም ካላቸው ተቋማት አንዱ ነው። የኮርፖሬሽኑ የስነ ምግባርና ቅሬታ መከታተያ አገልግሎት ሃላፊ ወይዘሮ ፀሃይ አድማሱ፥ የተቋሙን አመራሮችና ሰራተኞች ያካተተው ካውንስል ያዘጋጀው ስትራቴጂ በቦርድ ጸድቆ ከጥር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሚመራ የማኔጅመንትና የሰራተኛ ተወካዮችን ያካተተ ካውንስል አተገባበሩን በቋሚነተ በየወሩ እየተገናኘ እንደሚገመግምም ነው ወይዘሮ ፀሃይ ያብራሩት፡፡ በዚህም መመሪያ ላልነበራቸውና ለሙስና አሰራር ክፍት ለነበሩ አሰራሮች መመሪያ እንደተዘጋጀላቸው ገልጸዋል። በተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ ዝግጅትና ትግበራ በዝቅተኛ ደረጃ ከተፈረጁት መካከል ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ አንዱ ነው። የኤጀንሲው ስነ ምግባር መከታተያ ክፍል ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ደሱ እጅጉ እንዳሉት ስትራቴጂው ተግባራዊ ያልተደረገው አምስት የትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት የተቀናጀ የሙስና መከላከል ስትራቴጂውን በጋራ እንዲያቅዱ የወረደው አቅጣጫ አተገባበሩ ላይ መዘግየት በመፍጠሩ ነው፡፡ በኤጀንሲው ብቻ የሚገኙ አራት የስራ ሂደቶችን ነባራዊ ሁኔታ ያካተተ የሙስና መከላከል ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ለትምህርት ሚኒስቴር ቢላክም እስካሁን አለመጽደቁንም ነው ከፍተኛ ባለሙያ የገለጹት፡፡ የኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዳይሬክተሩ አቶ አክሊሉ እንዳሉት በዚህ ዓመት ተቋማቱ ሙስናን ለመከላከል ያከናወኗቸው ተግባራት ይገመገማሉ፤ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ደግሞ  ህብረተሰቡ በተቋማቱ ላይ ያለው የአገልገሎት እርካታ መመዘኛ ሆኖ ይካተታል። ኮሚሽኑ ስትራቴጂው በአግባቡ እንዲተገበር 227 ለሚሆኑ ተቋማት ከሚያደርገው ድጋፍና ክትትል በተጨማሪ ስትራቴጂውን የማስተዋወቅና የአተገባበር መመሪያዎችን የማዘጋጀት ተግባራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ዳይሬክተሩ ያረጋገጡት፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢህ አህመድ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ሙስና ቀይ መስመር መሆኑን ተረድተው በተቋማት የሃብት ምዝበራ እንዳይኖር ማሳሰባቸው  ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም