ኢትዮጵያና ኤርትራ ያደረጓቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር እየቀየሩ ነው

86
አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2010 ኢትዮጵያና ኤርትራ ያደረጓቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር ለመቀየር ሥራ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያ አየር መንገድም በነገው ዕለት 465 ተጓዦችን ይዞ ከሃያ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አስመራ ይበራል ተብሏል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በአገሪቱ ወቅታዊ የውጭ ግንኙነት ስራዎች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ አስመራ ተጉዘው ኤርትራን ከጎበኙ በኋላ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት አድርገው ሁለቱ አገራት የጋራ ጥቅሞችን የሚያስከብሩ የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያና ኤርትራ ያደረጓቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር ለመቀየር ሥራ መጀመሩን ነው አቶ ዓለም የገለጹት። በስምምነቱ መሰረትም ትላንትና በአዲስ አበባ ዳግም የተከፈተው የኤርትራ ኤምባሲ የስምምነቱ ትግበራ አንዱ አካል መሆኑ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያም በአስመራ ኤምባሲዋን ለመክፈት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንዳንድ የዝግጅት ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ቃል አቀባዩ አስረድተዋል። የአሰብ ወደብን ለመጠቀምም የመንገድ  የዝግጅት ሥራ በሁለቱም አገራት መካከል መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም ግብረ ኃይል መቋቋሙን ተናግረዋል። በግብረ ኃይሉም የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የማሪታይም አገልግሎት ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት ሎጂስቲክ አገልግሎት ተካተውበታል ብለዋል። ወደ አሰብ የሚወስደው መንገድ የጥገና ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው በድንበር አከባቢ የሚኖሩ የአፋርና የትግራይ ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲጀመር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም በነገው ዕለት 465 ተጓዦችን ይዞ ከሃያ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አስመራ በረራውን እንደሚጀምር ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአስመራ የቲኬት ቢሮ ከፍቷል፤ ሳምንቱን ሙሉ ከኢትዮጵያ አስመራ ቀጥታ በረራ እንደሚጀምርም ነው ያመለከቱት። ያም ብቻ ሳይሆን አየር መንገዱ 20 በመቶ የሚሆነውን የኤርትራ አየር መንገድ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል። ይህም በአገራቱ መካከል የሕዝበ ለሕዝብ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ የኢንቨስትመንት ፍሰት ላይም አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ከሳምንት በፊት የተጀመረው የስልክ አገልግሎትም የአገራቱ ሕዝቦች ግንኙነቱ እንዲጠናከር በማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል። አገራቱ አሁን ላይ የደረሱበት የሰላም ደረጃም ለሌሎች አገራት ምሳሌ የሚሆንና በተለይም በቀጣናው ላይ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ትልቅ ግብዓት መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ በአሁኑ ወቅት የተሟላ ግንኙነት መመስረታቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም