ሚኒስቴሩ የእንቦጭ አረምን ለማጥፋት የሚያግዝ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

72

አዲስ አበባ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) ትራንስፖርት ሚኒስቴር የእንቦጭ አረምን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከ11ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።

ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር ያደረገውን የገንዘብ ድጋፍ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ለአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ አስረክበዋል።

በርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ ሚኒስቴሩ የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በባህር ዳር ከተማ መገምገሙን ወይዘሮ ዳግማዊት አስታውሰዋል።

በጉባኤው ማግስትም የተቋሙ ሠራተኞች ''የሕዳሴ ግድብ ያለ ዓባይ፤ ዓባይም ያለ ጣና አይታሰብም፤ በህብር እንቦጭን ከጣና ላይ እናስወግድ'' የሚለውን ዘመቻ በመቀላቀል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።

በዛሬው ዕለትም ሚኒስቴሩ በሥሩ ካሉ ተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 11ሚሊዮን 728 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

"ድጋፉ በቂ  ባይሆንም አንድነታችንን፣ መተሳሰባችንንና መደጋገፋችንን አጉልቶ ያሳያል" ያሉት ሚኒስትሯ፣ የተጀመረው ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው " የተደረገው ድጋፍ ጣና የሁሉም እንደሆነና ሁሉም በባለቤትነት የሚሳተፍበት መሆኑ ያሳየ ነው " ብለዋል።

በተለይ ሚኒስቴሩ በአካል በመገኘት አረሙን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ከመቀላቀል ባለፈ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ፈር ቀዳጅ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ለተደረገው ድጋፍ በክልሉ ስም ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዶክተር ፋንታ፣ የሚኒስቴሩ አስተዋጽኦ ለሌሎች ተቋማት አርአያ እንደሚሆን ተናግረዋል።

''እንደ አገር አንድ ላይ ከተሰራና እንደ ህዝብ በአንድ ላይ መቆም ከተቻለ የማይገፋ ችግርና የማይወጣ ዳገት የለም'' ሲሉም አክለዋል።

የተደረገው ድጋፍ በተለይ በአሁኑ ወቅት መከፋፈላችንንና መለያየታችንን ለሚናፍቁ ሁሉ ሁሌም እጅ ለእጅ መያያዛችንን ያሳያል" ብለዋል።

ጣናን መነሻ በማድረግ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ባሉ ሐይቆች የተጋረጠውን አደጋ ለማስወገድ ጥናት ተካሂዶ ወደእንቅስቃሴ መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ ናቸው።

ዶክተር አብርሃ እንዳሉት በየቀኑ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በጉልበታቸው የእንቦጭ አረሙን ለማጥፋት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ይህን በህብረተሰቡ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባሻገር ብርታት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በድጋፍ ርከክቡ ላይ "ደማችን ለወገናችን'' በሚል መርህ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ወገንተኝነትን ለማሳየት ያለመ የደም ልገሳ መረሃ ግብር ተካሂዷል።

በመርሃግብሩም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ደም በመለገስ ለሠራዊቱ አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም