የአገራቱ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ እንዲጠናከር የበኩላችንን እናበረክታለን.... የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች

55
ሰመራ ሀምሌ 10/2010 በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ እንዲጠናከር የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በአፋር ክልል  የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የሎግያ ነዋሪ ወይዘሮ ሁዳ አብዱራማን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የአገራቱ መሪዎች የፈጠሩት አዲስ ግንኙነትና የሥራ ጉብኝት ሻክሮ የቆየውን የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ወደነበረበት መልሶታል፡፡ አገራቱ በዚህ ፍጥነት ግንኙነታቸውን ያሻሽላሉ ብለው እንዳልገመቱ የገለፁት አስተያየት ሰጪዋ፣ "ይህም በመንግስታቱ መካከል ለዘመናት የነበረው አለመተማመንና የጥርጣሬ መንፈስ መቀየሩን ያሳያል" ብለዋል፡፡ አገራቱ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በአሁኑ ወቅት የጀመሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በቀጣይም በህዝብ ለህዝብና በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገለጸዋል። "ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዲፕሎማሲዊ መስክ እያመጡት ያለው ስኬት ብቃትቸውን ያሳያል" ያሉት ደግሞ የሰመራ ከተማ ነዋሪ ሼክ አብዱሰመድ አልዩ ናቸው፡፡ አገራቱ ከዓመታት በኋላ ቅራኔያቸውን ፈተው ወደሰላም መምጣታቸው ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጠናው አገራት ተባብሮ የመልማት ተስፋን እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል። የሎግያ ከተማ ነዋሪ ሼክ መሃመድ ደርሳ በበኩላቸው የኢትዩጵያና የኤርትራ ህዝብ ግንኙነት እንደገና የሚጀመርበትን ቀን በጉጉት ይጠብቁ እንደነበረና ሰሞኑን በተፈጠረው ሰላም መደሰታቸውን ገልጸዋል። በተለይም ጠቅላይ ሚስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ግንባር ቀደም ተነሳሽነቱን ወስደው ከኤርትራ ጋር የነበረው አለመግባባትና ቅራኔ ያለሦስተኛ ወገን ጣልቃገብነት እንዲፈታ ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና አመስግነዋል፡፡ አገራቱ የፈጠሩትን ስምምነት ተከትሎ የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ኤምባሲውን እንደገና መክፈቱ  የህዝቦችን መልካም ወዳጅነት ለማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል። "ሰላም መውረዱ በተለይ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱ አገራት ህዝቦችን በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ ያደርጋል"  ብለዋል፡፡ እንደ ሼህ መሀመድ ገለጻ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ስምምነት በመሰል ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ አገራትም መልካም ተሞክሮ ይሆናል፡፡ በአገራቱ መሪዎች መካከል አሁን የተፈጠረው እውነተኛ የወንድማማችነት መንፈስ  ዘላቂ እንዲሆንና ግንኙነቱ እየሰፋና እየጠነከረ እንዲሄድ  የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም