የሆስፒታሎች የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እያሳየ ነው

109
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2010 በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆስፒታሎች በሚሰጡት የአገልግሎት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያመጡ እንደሆነ የአዲስ አበባ የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ። ባለስልጣኑ ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን የጀመረውን የቁጥጥር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። ባለስልጣኑ ፍተሻና ቁጥጥር ያካሄደባቸውን የጤና ተቋማት በተመለከተ ባቀረበው የኦዲት ሪፖርት ከዘርፉ ባለሙያዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በመዲናዋ በእስፔሻሊቲ ማዕከልነት ካሉት 22 ሆስፒታሎች መካከል በ2009 ዓ.ም 12ቱ በአረንጓዴ ደረጃ የነበሩ ሲሆን ዘንድሮ 18ቱ ወደ አረንጓዴ ደረጃ ተሸጋግረዋል። የአገልግሎት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ግብረ መልስ ተሰጥቷቸው ማስተካከያ ባላደረጉት ላይ ርምጃ ተወስዷል። ሆስፒታሎች መያዝ በሚገባቸው የአልጋ ቁጥር፣ በባለሙያ ስብጥር፣ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት በመስጠት ረገድ መሻሻል በማሳየታቸው የአገልግሎት ደረጃቸው ተሻሽሏል። የጤና ተቋማት ከስታንደርድ አኳያ በአረንጓዴና ቢጫ ደረጃ ተለይተው የተፈረጁ ቢሆኑም ውጤታቸውን መሰረት ያደረገ የአገልግሎት ጥራት ክፍተታቸውን በመለየት ማሻሻያ ማድረግ መቻላቸው ተጠቁሟል። በተሟላ ግብአት፣ የጥራት ደረጃ በዘመናዊ የህክምና ቴክኖሎጂ በመታገዝ አገልግሎት መስጠትና ደረጃቸውን የጠበቁ የላቦራቶሪና የምርመራ ግብዓቶችን በመያዝ ረገድ መሻሻል አሳይተዋል። በየጊዜው ከፍተኛ ለውጦች ቢመዘገቡም አገልግሎታቸውና የጥራት መጠናቸውን ለማወቅ በ632 የጤና ተቋማት ላይ ክሊኒካል ኦዲት ቁጥጥር ተደርጎ በ72ቱ ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው እርምጃ ተወስዷል። በችርቻሮ የመድኃኒት ድርጅቶችም የኦዲት ቁጥጥር በ312ቱ ላይ ተሰርቶ በ32ቱ ላይ የተለያየ እርምጃ ተወስዷል። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አለምፀሃይ ጳውሎስ እንደተናገሩት፤ አገራዊ የጤና ተቋማት ደረጃ ወጥቶ ወደ ተግባር ከተገባበት ጊዜ አንስቶ በተቋማቱ በሚደረገው ቁጥጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጦች እየተመዘገቡ መጥተዋል። በ2006 ዓ.ም ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር ከ50 በመቶ በታች ሆነው ስጋት ዝቅተኛ የሆነውን የቀይ ደረጃ ይዘው የነበሩ የጤና ተቋማት ቁጥር 122 እንደነበር አስታውሰዋል። በተደረገው የቁጥጥር ስራ በአሁኑ ወቅት አንድም ተቋም ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር ከ50 በመቶ በታች እንደማይገኝ የተናገሩት ወይዘሮ አለምፀሀይ 97 በመቶ የሚሆኑት በአረንጓዴ ደረጃ፣ ቀሪዎቹ ሶስት በመቶ የሚሆኑት በቢጫ ደረጃ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ውጤቱ እንዲመዘገብ የጤና ተቋማቱ ባለስልጣኑ የሚያደርገውን የቁጥጥር ስራ በማገዛቸው እንደሆነ ተናግረዋል። የጤና ቁጥጥር ባለሙያዎች ለተቋማቱ ተገቢውን እገዛና ክትትል በማድረጋቸው መሆኑም ተገልጿል። የአዲስ አበባ ጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ብቃት ማረጋገጥና ቁጥጥር ዳይሬክተር ሲስተር በድሪያ ሁሴን በበኩላቸው በተሰራው የቁጥጥር ስራ የጤና ተቋማት የተሻለ ደረጃ ላይ በመገኘት ለህብረተሰቡ በሚሰጡት አገልግሎት ለውጥ ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል። በተደረጉት የቁጥጥር ስራዎች 90 በመቶ የሚሆኑት የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም 10 በመቶ የሚሆኑት የጤና ተቋማት አገልግሎት ከመስጠት አኳያ አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች እንደሚስተዋልባቸው ተገልጿል። ለችግሩ መሰረታዊ መፍትሄ ለማምጣት የጤና ባለሙያዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም