የሰሜን ዕዝ የመገናኛ ሥርዓት እንዲቋረጥ እና በዕዙ ላይ ጥቃት እንዲፈፀምበት ሲያመቻቹ የነበሩ ጀነራል መኮንኖች ከነግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ሥር ዋሉ

97

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2013(ኢዜአ) የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር የሚኖረው የመገናኛ ሥርዓት እንዲቋረጥ በማድረግ በጁንታው የሕዋሓት የጥፋት ቡድን ጥቃት እንዲፈፀምበት ሲያመቻቹ የነበሩ ጀነራል መኮንኖች ከነግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫው በመንግሥት፣ በሕዝብ እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት የተጣለባቸውን አደራ እና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው የጁንታው ሕወሓት ሴራ አካል በመሆን የአገር ክህደት ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እና የበታች ሹማምንቶች በድምሩ 17 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ከጁንታው ሕወሓት ጋር በመጣመር ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በትግራይ ክልል የሚገኘው የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር የሚኖረው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥና የዕዙ የመገናኛ ሥርዓት ለጁንታው የሕዋሓት ወንበዴ ቡድን እንዲመቻች በማድረግ የተጠረጠረው ሜጀር ጀነራል ገብረመድህን ፈቃዱ ወይም በቅጽል ስሙ ወዲ ነጮ የተባለው ተጠርጣሪ በአገር ክህደት ወንጀል ከነግብረ አበሮቹ በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል።

የአገር ክህደትን በመፈጸም በዋነኝነት የተጠረጠረው ሜጀር ጀነራል ገብረመድህን ፍቃዱ ከለውጡ በፊት በአገር መከላከያ ሠራዊት የአጋዚ ኮማንዶ እና ልዩ ኃይሎች አዛዥ የነበረ ሲሆን፣ በሠራዊቱ ውስጥም በተለያዩ የሥራ እርከኖች ያገለገለ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ለውጡን ተከትሎም በአገር መከላከያ ሰራዊት የመገናኛ መምሪያ ኃላፊ በመሆን ሲሰራ እንደነበር አስታውሷል።

ይሁንና ከመንግሥት፣ ከሕዝብና ከአገር መከላከያ ሰራዊት የተጣለበትን ከባድ አደራና ኃላፊነት አገር ለማፍረስ እና ለማተራመስ ከሚንቀሳቀሰው የጁንታው ሕወሓት የሴራ አካል በመሆን የሰሜን እዝ ከማዕከል ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥ እና በከሃዲዎች ጥቃት እንዲፈፀመበት ከማድረጉም በላይ፤ በውስጣቸው ቦምቦች እና የሚሳኤል መሳሪያዎችን የያዙ 11 ሳጥኖች የግንኙነት መሳሪዎች ናቸው በሚል ሽፋን ወደ ትግራይ የጁንታው ቡድን ለመላክ ሲዘጋጅ ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በላከው መግለጫ አመልክቷል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ባደረጉት ጠንካራ ክትትል እና ባካሄዱት ኦፕሬሽን ተጠርጣሪው ሜጀር ጀነራል ገብረመድህን ፈቃዱን ጨምሮ ሌሎች ጀነራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እና የበታች ሹማምንቶቻቸው በድምሩ 17 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል።

በቀጣይም ከጁንታው የሕወሓት የጥፋት ቡድን አገር የማተራመስ እና የማፍረስ ሴራ እንዲሁም በአገር ክህደት ወንጀል የተሳተፉትን እና በየትኛውም የኃላፊነት ደረጃ እና መዋቅር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መግለጹን ኢብኮ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም