የተማሪዎችን የፈጠራ ውጤቶች ተግባራዊ ለማድረግ የባለሃብቶች ትብብር ወሳኝ ነው

74

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1/2013 (ኢዜአ) ተማሪዎች የሚያፈልቋቸውን ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶች ተግባር ላይ ለማዋል የባለሀብቶች ትብብር እንደሚያስፈልግ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ስቲም ፓዎር ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር የዓለም የሳይንስ ቀንን በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብሯል።

የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሚኒስቴሩ እያደረገ ባለው የስርአተ ትምህርት ለውጥ ተማሪዎች ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ግንዛቤ እንዲይዙ ትኩረት ተደርጓል።

ይህም ተማሪዎች በየክፍል ደረጃቸው የሳይንስ ክህሎታቸው እየዳበረ ሲሄድ የፈጠራ ውጤቶችን እንዲያወጡ የሚያበረታታ መሆኑ ነው የተገለጸው።

የፈጠራ ሥራዎችን የሚያበረክቱ ተማሪዎችን ማፍራት ብቻ በቂ አለመሆኑን ያነሱት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ የፈጠራ ሥራውን ተግባር ላይ ማዋል ወሳኝ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

"የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ተግባር በመቀየር ለማህበረሰቡ ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ የባለሃብቶችና የሥራ ፈጣሪዎች ትብብር ያስፈልጋል" ብለዋል።

እስካሁን ባለው በተማሪዎች የሚሰሩ የፈጠራ ውጤቶች ብዙም ተግባር ላይ አለመዋላቸውን ሚኒስቴሩ እንደሚያምን ገልጸው፤ በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የስቲም ፓዎር በኢትዮጵያ ተወካይና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ቅድስት ገብረአምላክ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ተማሪዎች ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ የሳይንስ ትምህርትን በተግባር እየተማሩ እንዲመጡ ቤተሙከራዎችን የማቋቋም ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን 43 የቤተሙከራ ማዕከላት የተቋቋሙ ሲሆን በተያዘው ዓመት አጋማሽም 51 ለማድረስ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የምጣኔ ሃብት እድገት ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍም በተማሪዎች ላይ በሳይንስ ዘርፍ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ስቲም ፓዎር በዛሬው መርሃ ግብር ተማሪዎችን በፈጠራ ሥራቸው አወዳድሮ ታብሌት ኮምፒውተር የሸለመ ሲሆን በቀጣይም የፈጠራ ሥራዎች ወደ ተግባር የሚለወጥበት ሁኔታ እንደሚመቻች ተገልጿል።

በፈጠራ ሥራቸው የተሸለሙ ተማሪዎችም ሽልማቱ በቀጣይ ለአገራቸው የተሻለ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤት ለማበርከት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።

የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ናትናኤል አሸናፊ ከንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን መሸጥ የሚያስችል ማሽን ሰርቶ በማቅረብ ከተሸለሙ ተማሪዎች ውስጥ አንዱ ነው።

ዓለም በአሁኑ ጊዜ በተራቀቀ መንገድ እየሄደችበት ያለውን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የፈጠራ ውጤት ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የማድረግ ህልም እንዳለውም ተማሪ ናትናኤል ገልጿል።

ህልሙ እውን ይሆን ዘንድ እውቀቱን ተጠቅሞ የሚፈጥራቸውን የሳይንስ ውጤቶች ባለሃብቶች በገንዘብ በመደገፍ ማህበረሰቡን እንዲጠቅሙ ጠይቋል።

በጸረ -አረምና ሌሎች ኬሚካሎች መርጫ የፈጠራ ውጤቷ ተሸላሚ የሆነችው የ12 ክፍል ተማሪ ሰርካለም ደለለኝ በበኩሏ እንዳለችው ሽልማቱ የበለጠ የፈጠራ ውጤት እንድታፈልቅ አነሳስቷታል።

ሥራዋ ተግባር ላይ እንዲውል አቅም ያላቸው ባለሃብቶችና ሥራ ፈጣሪዎችን ትብብርን ጠይቃለች።

የዓለም የሳይንስ ቀን በኢትዮጵያ ለ5ኛ ጊዜ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን ተማሪዎችን በሳይንስ፣ ኢንጅነሪንግና ሒሳብ ትምህርቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የማበረታታት ዓላማ አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም