በጣና ሀይቅ ሙላት ሰብል ለወደመባቸው አርሶ አደሮች ተተኪ ዘር እየተሰራጨ ነው

70

ጎንደር፣ ጥቅምት 30/2013 (ኢዜአ)  የጣና ሀይቅ ሞልቶ ባደረሰው መጥለቅለቅ ሰብል ለወደመባቸው አርሶ አደሮች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የተገዛ ተተኪ ዘር እየተሰራጨ መሆኑን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ 

በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ጀንበሩ ደሴ ለኢዜአ እንደገለጹት የዘር ስርጭቱ እየተካሄደ ያለው ሀይቁ በሚያዋስናቸው በማእከላዊና በደቡብ ጎንደር ዞኖች በ6 ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ነው፡፡

ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በ9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዛ 1 ሺህ 935 ኩንታል የሽንብራ፣ የጤፍ፣ ምስርና ስንዴ ተተኪ ዘር ለአርሶ አደሮቹ እያሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል ።

ተተኪ ዘሩ ከ 6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል ።

እየተሰራጨ ያለው ተተኪ ዘር 5 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል ።

አርሶ አደሮቹ በቀሪ እርጥበትና በአነስተኛ መስኖ በመታገዝ እንዲያለሙ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ተተኪ ዘር ላልቀረበላቸው ተጎጂ አርሶ አደሮች 5 ሺህ 900 ኩንታል የአካባቢ ዘር ገዝተው መጠቀም እንዲችሉ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የተመደበላቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ።

"ሀይቁ ሞልቶ ባደረሰው መጥለቅለቅ 6 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ሰብል እስከ 70 በመቶ ጉዳት ደርሶበታል" ያሉት ደግሞ በማእከላዊ ጎንደር ዞን የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ አደጋ መከላከልና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ አቶ አገኘሁ አስማረ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም