የትግራይ ህዝብ የህወሓት የጥፋት ቡድን ለፖለቲካ ትርፍ ሲል ሊያደርሰው ከሚችለው ጥፋት ሊጠነቀቅ ይገባል- ትዴፓ

94

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2013 ( ኢዜአ) የትግራይ ህዝብ የህወሓት የጥፋት ቡድን ለፖለቲካ ትርፍ ሲል ሊያደርሰው ከሚችለው ጥፋት ሊጠነቀቅ እንደሚገባው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ገለጸ።

የህወሃት ጁንታ ከሰሜን ዕዝ የዘረፋቸው ሮኬቶችን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን የኢፌዴሪ አየር ኃይል በወሰደው እርምጃ መውደሙን ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ መግለፃቸው ይታወሳል።

የጥፋት ቡድኑ እነዚህን መሳሪያዎች በመያዝ በንጹሃን ኢትዮጵያዊያን ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀስ እንደነበረም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመግለጫቸው በጁንታው ላይ የሚሰነዘረው የምድርም ሆነ የአየር ላይ ጥቃት በህዝብ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በጥንቃቄና በተመረጡ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የዚህ ጁንታ ዘራፊ ቡድን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጠነስሳቸውን ሴራዎች የትግራይ ህዝብ ላይ ጥፋትና ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ብለዋል የትዴፓ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ሃይሌ።

የህወሃት ቡድን ከአመጣጡም ጀምሮ በሴራ የተካነ፣ በትግል አጋሮቹም ሆነ ደጋፊዎቹ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የማይራራ መሆኑ ይታወቃል ብለዋል።

ይሄው ጁንታ አሁን ላይ እየተሸነፈ በመሆኑ በትግራይ ህዝብ ላይ በተካነበት ሴራ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጥፋት ሊያደርስ ስለሚችል ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል።

ቡድኑ በትግራይ ክልል ያሉ ቅርሶች ላይ፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሰዎች በተሰበሰቡባቸው ስፍራዎች ላይ ጥፋት አድርሶ ሌላ አካል እንዳደረገው ለማስመሰል ስለሚጥር ህዝቡ በጥንቃቄ ሊከታተለው ይገባል ብለዋል።  

ዘራፊው ቡድን የአገር ዳር ድንበር በማስከበር ተልእኮ ላይ በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈፀሙም ለከሃዲነቱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲል ዘራፊው ወስዷቸው የነበሩ ሮኬቶችን ማምከኑ ጥሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ሙሉብርሃን በህዝብ ላይ ሌላ ጥፋት እንዳያደርስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ቡድኑ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ለትግራይ ህዝብ ያበረከተው ነገር ሳይኖር ለራሱ ጥቅም ብቻ ሲሰራ የኖረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዘራፊ ቡድኑ አሁን እየተጠቀመባቸው ያሉ ሚዲያዎች ስለልማት፣ ዴሞክራሲና ስለህዝብ ጥቅም ሳይሆን ስልጣኑን ለማስጠበቅና የህዝቡ ተቆርቋሪ በመምሰል የሃሰት ወሬዎችን ስለሚያሰራጭ እንዳይቀበሉት መክረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ጁንታውን ከማስወገድ ውጭ የትግራይን ህዝብ የመጉዳትም ሆነ የማጥቃት ዓላማ እንደሌለውም ህዝቡ ሊያወቅ ይገባል ነው ያሉት አቶ ሙሉብርሃን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም