እሥራኤል አንበጣን ለመከላከል የሚያግዙ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ልትልክ ነው

45

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2013 ( ኢዜአ) እሥራኤል አንበጣን በመከላከል እገዛ የሚያደርጉ ባለሙያዎችን በቀጣይ ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ እንደምትልክ የአገሪቱ ባለሥልጣን አስታወቁ።

የእሥራኤል የደህንነት ምክትል ሚኒስትር ጋዲ ይቫርካን ለኢዜአ እንዳሉት አገራቸው በኢትዮጵያ የተከሰተውን አንበጣ ለመከላከል በሚካሄደው እንቅስቃሴ አጋርነቷን ለማሳየት ባለሙያዎቿን ትልካለች።

ኢትዮጵያ የእስራኤል ወዳጅ አገር በመሆኗ በችግር ጊዜ በአጋርነቷ እንደምትቀጥል ገልጸው፤ ውሳኔው ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በመነጋገር መደረጉን  ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ አንበጣን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት በስልጠናና በቴክኖሎጂ እንደሚያግዙ አመልክተዋል።

እሥራኤል በቀጣይም በሌሎች ዘርፎች ትብብር ማድረጓን እንደምትቀጥል ምክትል ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

አገሮቹ በምጣኔ ሃብት፣ በማህበራዊና በፖለቲካ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል።

እሥራኤል በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተውን እሳት ለመቆጣጠር ድጋፍ እንዳደረገች ይታወሳል።

የኢትዮጵያና እሥራኤል የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ1955 የተጀመረ ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው የበረሃ አንበጣን መከላከልና መቆጣጠር ካልተቻለ በቀጠናው ሊያደርስ የሚችለው ተጽእኖ ከፍተኛ እንደሚሆን ባለሙያዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

መንግሥት በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣በትግራይ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ለመከላከል እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም