የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን ለዲፕሎማቶች በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስለሚገኘው የህግ ማስከበር ስራ ማብራሪያ ሰጡ

90

ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለዲፕሎማቶች በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስለሚገኘው የህግ ማስከበር ስራ ትናንት ማብራሪያ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ህወሃት በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም የጦር መሳሪያ ለመዝረፍ መሞከሩን በማብራሪያቸው ገልጸዋል።

የህወሃት ዘራፊ ቡድን ጥቃት በመክፈት የዘረፈውን መሳሪያ በመጠቀም በቅርብም ሆነ በሩቅ የሚገኙ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እንደሚችል መፎከሩንም ለዲፕሎማቶቹ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።

ጥቃት የተፈጸመበት የአገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ህዝብ ጎን በመሆን የአምበጣ መንጋ ሲከላከል፣ የአርሶ አደሩን ምርት ሲሰበስብና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማልማት እየሰራ የሚገኝ እንደነበር ጠቅሰዋል።

የህወሃት ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ከፈጸመው ጥቃት በተጨማሪ የተለያዩ የፌዴራል መንግስት ተቋማትን ሲጠብቁ በነበሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት መፈጸሙንም ገልጸዋል።

ቡድኑ ይህንን ጥቃት ሲፈጽም ህብረተሰቡ ለመከላከል ጥረት ማድረጉንም ጠቁመዋል።

የህወሃት ዘራፊ ቡድን አዲስ የተቀየረውን የብር ኖት ጭነው የሄዱና አሮጌውን ይዘው ለመመለስ አውሮፕላኖችን ለማገት መሞከሩንም ገልጸዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብሔርንና እምነትን መሰረት ያደረገ ሁከትና ሽብር ሲፈጥር እንደነበር አስታውሰው፤ ለዚህ ድርጊት የሚያሰማራቸውን ሃይሎች ሲያሰለጥና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አብራርተዋል።

አሁን እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ሶስት ዓላማ እንዳለው በመግለጽ፤ የመጀመሪያው ዓላማ ድንገተኛ ጥቃት የተከፈተበትን የመከላከያ ሰራዊት ከዘራፊው ቡድን መታደግ እንደሆነ ገልጸዋል።

ቡድኑ ኢትዮጵያንም ሆነ ጎረቤት አገሮችን እንዳያጠቃ አቅም የማሳጣት ስራ በመስራት በህዝብና በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሌላው የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና ህገመንግስትን ማስከበር እንዲሁም ህዝብን ነጻ ማውጣት እንደሆነ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም