በሰሜን ሸዋ በመስኖ ልማት ከ14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ

113
ደብረ ብርሃን ኀምሌ 10/2010 አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባለፈው የበጋ ወቅት በመስኖ ከለማው መሬት ከ14  ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ባለሙያ ወይዘሮ ሁሉምታዬ ዘነበ ለኢዜአ እንደገለጹት ምርቱ የተሰበሰበው በዞኑ 24 ወረዳዎች በመስኖ ከለማው 89 ሺህ 332 ሄክታር መሬት ላይ  ነው። የተሰበሰበው ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከአንድ ሚሊዮን 94 ሺ ኩንታል በላይ  ብለጫ አለው፡፡ ለምርቱ መጨመርም አርሶ አደሩ ጥቅሙን አውቆ በትጋት መስራቱ ፣ የገበያ ትስስር በመፈጠሩና መስኖ ልማት በዘመናዊ ቴክኖሎጅ  እንዲታገዝ በመደረጉ ተጠቃሽ ምክንያት ነው። በልማቱ የተሳተፉ  257 ሺህ 153 አርሶ አደሮችም እስከ ሶስት ዙር በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀወት ወረዳ የየለን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞገስ ወንድአፈራሁ እንዳሉት በባለሙያ ታግዘው በየአመቱ በሚያካሂዱት የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው የበጋ ወቅትም በአንድ ተኩል ሄክታር መሬት ላይ 340 ኩንታል የሽንኩርትና የማሽላ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ማሽላውን ለቀለባቸው አስቀምጠው ከሽንኩርት ሽያጭ ያገኙትን 350 ሺህ ብር በባንክ መቆጠባቸውን አስረድተዋል፡፡ በዞኑ የሞጃና ወደራ ወረዳ የሳሲት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተገኝ ሀብቴ በበኩላቸው በመስኖ ካለሙት አንድ ሄክታር መሬት 70 ኩንታል የሽንኩርትና የምስር ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስርም ምርቱን በመሸጥ 109 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም