እምቦጭን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እየሰራን ነው-የጎንደር ዙሪያ ነዋሪዎች

73

ባህርዳር፣ ጥቅምት 27/2013 (ኢዜአ) "መንግስት ያሳየው ተነሳሽነት የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እንድንሰራ አድርጎናል" ሲሉ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።


በወረዳው የላምባ አርባእቱ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ነጋ ያለው ለኢዜአ እንደገለጹት የእምቦጭ አረም እንደተከሰተ ልምላሜውን በመመልከትና እንደ ጠቃሚ ሳር በመቁጠር ለእንስሳት መኖነት ይጠቀሙበት ነበር ።


በሂደት አረሙን የተመገቡ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች በበሽታ እየተጠቁ ለሞት እንደሚዳረጉ ተናግረዋል ።
አረሙ የምርት መቀነስ እንዲያጋጥም ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።


"እምቦጭ አርሶ አደሩን ለድህነት የዳረገ ዋና ጠላት መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ ችለናል" ብለዋል ።

በተለይም መንግስት እንቦጭን ለማስወገድ ያሳየው ተነሳሽነት አረሙን ነቅሎ ለማጥፋት በቁርጠኝነት እንድንሰራ አስችሎናል ብለዋል።


"በመንግስት እገዛ አረሙን የማስወገድ ዘመቻ ተጀምሯል" ያሉት አርሶ አደር ነጋ ከሌሎች ስራዎች ጎን ለጎን አረሙን የማጥፋት ስራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል ።


የእምቦጭ አረም ለአሳ ምርትና ለከብቶች መኖ መቀነስ ምክንያት ከመሆኑ ባለፈ የሃይቅ ላይ የጀልባ ትራንስፖርት እንዲስተጓጎል ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ ገዳም አስፋው ናቸው።


የአካባቢው ማህበረሰብ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት አረሙን ለማጥፋት ጥረት ማድረጉን አስታውሰዋል ።


መንግስት በዚህ ዓመት አረሙን ለማስወገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ ነዋሪው በበለጠ ተነሳሽነት አረሙን ለማጥፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።ህብረተሰቡ አረሙን ለማስወገድ በሰራው ስራ አበረታች ውጤት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል ።


በአማራ ክልል የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ እምቦጭ በተከሰተባቸው 30 ቀበሌዎች በየቀኑ ከ10 ሺህ በላይ የኀብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የማስወገድ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።


መንግስት የእምቦጭ ማስወገድ ብሄራዊ ንቅናቄ ዘመቻ መርሃ ገብር በመንደፍ ወደ ተግባር በመግባቱ አረሙን የማጥፋት ስራው ወጤት እየታየበት መሆኑን ጠቅሰዋል።


"መንግስት እምቦጭን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ከማቅረብ ባሻገር ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ በማድረጉ ለተመዘገበው ውጤት አስተዋጾ አበርክቷል" ብለዋል ።


እምቦጭ እያደረሰ ያለውን ጥፋት ለመታደግ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ ከቀጠለ አረሙን በዘላቂነት ለማጥፋት እንደሚቻል ተናግረዋል።


በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ድረስ ከእምቦጭ ሙሉ በሙሉ ነጻ የሆኑ ቀበሌዎችን ቁጥር 15 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም