ቋሚ ኮሚቴው የማዕድን ነዳጅና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን ሪፎርም ለኢኮኖሚው ልማት አስፈላጊ መሆኑን ገለጸ

99

አዳማ፣ ጥቅምት 27/2013(ኢዜአ ) የማዕድን ነዳጅና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን የሀገሪቷን የኢኮኖሚ ልማት መደገፍ የሚያስችለው ሪፎርም ማካሔድ እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ። 

የኮርፖሬሽኑን አሰራር ለማሻሻል በሚያስችሉ አቅጣጫዎችና የህግ ማእቀፎች ላይ ያተኮረ ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሔደ ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ውይዘሮ ፈቲያ ዩሱፍ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ተቋሙ ያለውን አቅም ለሀገር ኢኮኖሚ ልማትና ለህዝቦች ተጠቃሚነት ለማዋል ሪፎርም ያስፈልገዋል።

ተቋሙ በመንግስት የልማት ድርጅት ስር መቆየቱን የገለጹት ሰብሳቢዋ ከባለሃብቶች፣ ከክልሎች ጋርና በራሱ የሚያከናውናቸውን ስራዎች በጥናት ለይቶ እንዲያቀርብ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

የሚያጋጥሙ ችግሮችንም ከምክር ቤቱ ባለፈ በኮርፖሬሽኑ አቅም የሚፈቱትን በዝርዝር በመለየት በተለይ ከስልጣንና ተግባር አንፃር የተከናወኑትንና ያልተከናወኑትን በመለየት ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ቢሰራበት ኖሮ ለሀገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሚናው የጎላ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ፈቲያ ከህግ ማእቀፎችና አሰራሮች አንፃር በርካታ ክፍተቶች የሚስተዋሉበት በመሆኑ ችግሮቹን በጥናት ለመፍታት አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቁመዋል።

በዘርፉ ከሚታዩት ቁልፍ ችግሮች ውስጥ በወቅታዊ የፀጥታ ችግርና በኮሮና በሽታ ምክንያት የምርት ቦታዎች መቆምና ተቋሙ ከምርትና ምርታማነት በመገለሉ የተነሳ ህልውናውን ማስጠበቅ በማይችልበት ደረጃ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ሰይድ ናቸው።

"በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑን ከመፍረስ ለመታደግና ወደ ምርት እንዲመለስ ለማስቻል የአሰራር፣ የህግ ማእቀፎች ማሻሻያና ሪፎርም ያስፈልጋል" ብለዋል።

"ለዚህም ምክር ቤቱ የተቋሙን ህግና አሰራር ለመለወጥና ወደ ሪፎርም ለመግባት ድጋፍና ክትትል ሊያደርግልን ይገባል" ብለዋል።

የመድረኩ ዓላማም የምክር ቤት አባላቱና የቋሚ ኮሚቴ አመራሮች የኮርፖሬሽኑን ችግር ተገንዝበው በማሻሻያ ስራው ላይ አስፈላጊውን እገዛ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መሆኑን ገልጸዋል።

"በተያዘው የበጀት ዓመት ከውጭ የሚገቡትን የማዕድን ምርቶች በተለይም የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ግብዓት፣ የኢታኖል ማቀነባበሪያ ፕሮጀክት፣የመጠጥ ውሃ ማጣሪያ ማዕድን፣የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ልማት እንዲሁም በደለል ወርቅ ልማት በስፋት ለመሳተፍ አቅደን እየሰራን ነው" ብለዋል።

በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ የምክር ቤት አባላትና የቋሚ ኮሚቴ አመራሮችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም