በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ

61
ጎባ ግንቦት 3/2010 በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው በባሌ ዞን ለሰፈሩ ወገኖች የውሃ ማመላለሻ ቦቴዎችና የምግብ እህል ድጋፍ አደረጉ። በሪያድና ጅዳ ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን 6 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ የተገዙ ሁለት የውሃ ቦቴ ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ ሲያደርጉ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ 678 ኩንታል በቆሎና ዱቄት ለግሰዋል። በሪያድና ጅዳ የድጋፍ አስተባባሪ ኡስታዝ ራያ አባመጫ ተሽከርካሪዎቹን ትናንት ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት በባሌ ዞን የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች የውሃ እጥረት መኖሩን በመገንዘባቸው ድጋፉን አድርገዋል። በሪያድና ጅዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቀረበላቸው አስቸኳይ የድጋፍ ጥሪ መሰረት ድጋፉን ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። በተመሳሳይ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በግጭቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውንና በቀጣይም የተፈናቀሉ ዜጎች በቋሚነት እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል ። የባሌ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አብዱልቃድር ሁሴን በበኩላቸው በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለወገኖቻቸው ላደረጉት ድጋፍ  ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሰፈሩ ወገኖች የሚያጋጥማቸውን የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ለመፍታት የውሃ ማመላለሻ ቦቴዎቹ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዞኑ የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሐም ኃይሌ በበኩላቸው መንግስት ለተፈናቃዮች ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ለጋሽ አካላት እያደረጉት ያለው እገዛ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሰዌና ወረዳ "ቁኒ" ጊዜያዊ መጠለያ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አቶ ማህሙድ በከር ችግራቸውን ተገንዝበው ፈጠን ምላሽ ለሰጧቸው በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምስጋናቸው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም