በኢትዮጵያ የፈጠራ ውጤቶችን ሥራ ላይ ለማዋል ቪዛ እና ስቴምፓወር በጋራ መስራት የሚያስችል አጋርነት ፈጠሩ

79

አዲስ አበባ ጥቅምት 24/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የፈጠራ ውጤቶችን ሥራ ላይ ለማዋል ቪዛ እና ስቴምፓወር የተባሉ ድርጅቶች በጋራ ለመስራት የሚያስችል አጋርነት ፈጠሩ። 

ሁለቱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ቅንጅት መፍጠራቸውን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርገዋል።   

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ሚሊዮን ማቲዎስ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱን ጨምሮ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

ስቴምፓወር በኢትዮጵያ ባለፉት 13 ዓመታት 43 ማዕከላት የከፈተ ሲሆን በማዕከላቱ ተማሪዎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነርንግና ሂሳብ ችሎታቸውን  የሚያጎለብቱበት ፕሮጀክት ቀርጾ ሲተገብር ቆይቷል።   

በማዕከላቱ የፈጠራ ሥራዎችን ይዘው የሚመጡ ተማሪዎች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የቴክኒክ፣ የስልጠና እና አጋር በማፈላለግ ድጋፍ እንዲያገኙ የማመቻቸት ስራዎች እየተሰሩም ነው።    

የቴምፓወር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቅድስት ገብረአምላክ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ቪዛ ከተሰኘው ተቋም ጋር በመተባበር የፈጠራ ሥራ ያላቸውን ልጆች ወደ ተግባር የሚቀይሩበት መርሃ ግብር ቀርጾ እንቅስቃሴ ጀምሯል።    

መርሃ ግብሩ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ሥራ ፈጣሪዎች የሚደግፍ መሆኑን አብራርተዋል።  

በመርሃ ግብሩ መሰረት ቪዛ የተሰኘው ተቋም የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን የፈጠራ ሥራ ያላቸው ዜጎች ከገንዘብ አስተዳደር፣ አያያዝና የአዕምሮ ውጤታቸውን በምን መልኩ ሥራ ላይ ማዋል አለባቸው? የሚለው ላይ የክህሎት ስልጠና ይሰጣቸዋል።  

የፈጠራ ውጤቱን ሥራ ላይ ለማዋል ከባለሃብቶች ጋር ማገኛነት ሌላው ተግባር ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ የፈጠራ ባለቤቶቹ ፍቃድ እስኪያገኙ ድረስም ድጋፋችን አይቋረጥም ብለዋል።  

በየሦስት ወሩ ሲሆን መርሃ ግብሩ እስኪጠናቀቅ ድረሰ 4 ሺህ የፈጠራ ባለቤቶችን ለማሰልጠን እቅድ ተይዟል።  

በመርሃ ግብሩ ላይ የጾታ፣ እድሜና  የትምህርት ደረጃ ከግምት ውስጥ የማይገባ መሆኑን ጠቅሰው ዋናው የሚፈለገው ፈጠራው ስራ ላይ ሊውል የሚችል መሆኑ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።  

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት የዲጂታል ኢኒሼቲቭ አስተባባሪ ሜሪየም ሰኢድ በበኩላቸው ተቋማቱ የፈጠሩት አጋርነት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ ለወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራ አወንታዊ ሚና ይኖረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም