ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ገለጹ

94

ጋምቤላ፣ ጥቅምት 21/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ በገንዘብ ሆነ በሌሎች ጉዳዮች አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፍል ዝግጁ መሆናቸውን የፌደራል ፖሊስ የምዕራብ ዳይሬክቶሬት አባላት ገለጹ ።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሰሞኑን ለግብጽ በመወገን የህዳሴውን ግድብ አስመልክተው ያስተላለፉት የማስፈራሪያ መልዕክት እንዳስቆጣቸውም አባላቱ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በምዕራብ ዳይሬክቶሬት የዲቪዥን አንድ ምክትል አዛዥ ኮማንዳር ተሾመ ወርቁ ሠራዊቱ የህዝብና ሀገርን ሰላም ለመጠበቅ የተሰጠውን ግዳጅ በላቀ ቁርጠኝነት ለመፈጸም ዝግጁ ነው ብለዋል።

በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለግብጽ በመወገን ያስተላለፉት ማስፈራሪያ አዘል መልዕክት እንደ መላው ኢትዮጰዊያን ሁሉ የሠራዊቱ አባላትንም በእጅጉ እንዳስቆጣ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ካሁን በፊትም ለመውረር የሚሞከሩ ኃይሎች ሽንፈትን አከናንበው ከመመለስ ባለፈ ሀገሪቱ በማንም ተንበርካ እንደማታውቅ ለማንም የተሰወረ አይደለም ብለዋል።

በህዝብ ተሳትፎ የተጀመረው ታላቁ የህዳሴው ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ሠራዊቱ በገንዘብም ሆነ በማንኛውም ሁኔታ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

የህዳሴው ግድብ የሚገንባው በማንኛውም የውጪ እርዳታ ሳይሆን በህዝቦቿ ገንዘብና ጉልበት መሆኑን የተናገሩት ኮማንደሩ ከአሜሪካም ሆነ ከግብጽ በሚነዛ ወሬ አንበገርም ብለዋል።

"ቀደምት አባቶቻችን ከየትኛውም የውጪ ወራሪ ጠብቀው ያቆየዋትን ሀገር በአሁኑ ትውልድም አትደፈርም" ያሉት ደግሞ ሌላኛው የሠራዊቱ አባል ኮንስታብል ከፍያለው ጥላሁን ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ለመውጣት በእራሳቸው ገንዘብና ጉልበት እየተገነባ ባለው የህዳሴ ግድብ የሚቃጣን ጥቃት ለመመከት በላቀ ቁርጠኝነት ግዳጃቸውን ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል ለሰባተኛ ጊዜ በደሞዛቸው ቦንድ መግዛታቸውን ጠቁመው በቀጣይም ግድብ እስኪጠናቀቅ ከገንዘብ ድጋፍ ጀምሮ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ ኮንስታብል ከፋያለው ተናግረዋል።

ሌላው የሠራዊት አባል ኮንስታብል መኮንን እሸቱ በበኩላቸው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፍፃሜውን እስኪያገኝ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል።

በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ግብጽን በመወገን ኢትዮጵያዊያን በእራሳቸው ሀብትና ጉልበት እየገነቡት ያለውን የህዳሴው ግድብን አስመልክተው ላስተላለፉት የጥፋት መልዕክት ሳይንበረከኩ እስከ ግንባታው ፍጻሜ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም