በኦሮሚያ ክልል በኮቪድ-19 የተቀዛቀዘውን ቱሪዝም ለማነቃቃት ያለመ የመስህብ ስፍራዎች ጉብኝት እየተካሄደ ነው

63

አዳማ፣ ጥቅምት 21/2013( ኢዜአ) በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ቱሪዝም ለማነቃቃት ያለመ የመስህብ ስፍራዎች ጉብኝት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ነው።

መነሻውን ላንጋኖ ሀይቅ፤ መዳረሻው ሶፍ ኡመር ዋሻ በማድረግ “ኦሮሚያን እናስተዋውቃት” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ጉብኝት ለአራት ቀናት ይቆያል።

የአለም የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ የክልሉ የመስህብ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ የጉብኝቱ ዓላማ መሆኑ ተገልጿል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ሁሉም እንዲጎበኝ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በጸጥታ ችግር ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ከበደ፤ “ኦሮሚያ ቤታችሁ ናት ከኮሮና ጥንቃቄ ጋር መጥታችሁ ጎብኙን፣ ተዝናኑ፣ ሰርታችሁ አገራችሁን አሳድጉ” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮ ቱሪዝም፣ በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና በኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ትብብር የተዘጋጀው ይህ ጉብኝት በክልሉ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ያስተዋውቃል።

ጉብኝቱ በኦሮሚያ ካሉት አምስት መዳረሻ መስመሮች የስምጥ ሸለቆና ባሌ ሶፍ ኡመር ዋሻን ያካትታል።

የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች፣ የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣ የሀረና ደንና የሶፍ ኡመር ዋሻ እንደሚጎበኙ ታውቋል።

በጉብኝቱ ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአስጎብኚ ድርጅቶች እንዲሁም ከዘርፉ የተውጣጡ የሚመለከታቸው አካላትና የሚዲያ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም