ክልሉ በገቡት ውል መሠረት ያልሰሩ የ55 ባለሃብቶችን ፈቃድ ሰረዘ

83

አሶሳ ጥቅምት 20 / 2013(ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በገቡት ውል መሠረት ያልሰሩ የ55 ባለሃብቶችን ውል በማቋረጥ ፈቃዳቸውን መሰረዙን የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ገለታ ሃይሉ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የባለሀብቶቹ ወል የተረጠው  በክልሉ   ለረጅም ዓመት የያዙትን 29 ሺህ 025 ሄክታር መሬት በገቡበት ውል ሳያለሙ በመቆየታቸው ነው፡፡

በኢንቨስትመንት ስም ከቀረጥ ነጻ የወሰዷቸውን ማሽኖች ላልተገባ ዓላማ ሲያውሉ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ባለሃብቶቹ 385 ሚሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግው እንደነበር አስታውሰው በአግባቡ ቢንቀሰቅሱ 10 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ይጠበቅባቸው ነበር ብለዋል፡፡

አብዛኞቹ በግብርና ዘርፍ ተሰማርተው የነበሩት ባለሀብቶቹ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ ባደረገው ግምገማ አፈጻጸማቸው ከሚጠበቀው በታች በመሆኑ ውላቸው ተቋርጦ የወሰዱት መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የባለሃብቶቹ ውል ሰሞኑን እንዲቋረጥ የተደረገው በገቡት ውል መሠረት መሰረት ባለመስራታቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ በ2013 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለ91 ባለሀብቶች ፈቃድ መሠጠቱን አቶ ገለታ ተናግረዋል፡፡

ባለሀብቶቹ 47 ሺህ 086 ሄክታር መሬት መረከባቸውን አመልክተው  አብዛኞቹ በግብርና ዘርፍና የተወሰኑት ደግሞ   በእጣን ማምረት የተሠማሩ መሆናቸውን አስታወቀዋል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ ባለፈው ዓመት በግብርና ዘርፍ ለረጅም ዓመት ተሰማርተው ከአቅም በታች ሲሰሩ በቆዩ የ22 ባለሃብቶች ውል በማቋረጥ መሬታቸውን መንጠቁን በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም