የተመረቁት ፕሮጀክቶች ለከተማ ዕድገትና ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ

47

ድሬዳዋ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት መርቀው ሥራ ያስጀመሯቸው ፕሮጀክቶች ለከተማ ሁለንተናዊ ዕድገትና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው በድሬዳዋ አስተዳደር አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በዘመናዊው የኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ ለሚጀምሩት ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርጉም ገልፀዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ በ150 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት ድርጅትን ትናንት መርቀው ስራ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

በምርቃው ሥነ ሥርዓት ከተሳተፉ ነዋሪዎች መካከል አቶ መሀመድ ሙሴ እንዳሉት፤ ፓርኩ ለድሬዳዋ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት ዕድገት ወሳኝ ድርሻ ያበረክታል፤ የተቀዛቀዘውን ከተማ ወደ ቀድሞ የእድገት ይዞታው በመመለስ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው  ነው፡፡

እንደተረዳሁት በፓርኩ የተገነቡት ሼዶች ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምሩ ለ20 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ለከተማው ወጣቶች ትልቅ የምስራች ነው ያሉት ደግሞ ሊቀብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው ናቸው፡፡

ይህም የተማረውም ያልተማረውም ወጣት ሥራ ፍለጋ መሰደድን የሚያስቀርና ለወላጆችም ትልቅ የምስራች የሚያመጣ ልማት ነው፤ ሁላችንም በአግባቡ የምንጠብቀው ሃብት ሊሆን ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሥራ በጀመሩት አለም አቀፍ የጫማና የክር አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ሥራ ያገኘው ወጣት አሚን ሁሴን በበኩሉ ፓርኩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ አዳዲስ ባለሃብቶች ወደ ከተማ መጥተው ሥራ እንዲጀምሩ በማነቃቃት ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚያግዝ ተናግሯል።


በከተማ ተምረው ያለሥራ ተቀምጠው ለተለያዩ ችግሮች ለተጋለጡ ወጣቶች መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ የተናገረው ደግሞ ወጣት ሰለሞን ታዬ ነው።

ፓርኩ በተገነባበት አካባቢ የሚገኘው የመልካ ጀብዱ ቀበሌ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱላሂ አብዶ ፓርኩ ለልማቱ ለተነሱ የገደንሰር ገጠር ቀበሌ አርሶአደሮችና ልጆቻቸው ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ወደ ፓርኩ የሚመጡ ባለሃብቶች በስራቸው እንዲረኩ አስፈላጊው ድጋፍና ጥበቃ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በድሬዳዋ የአዱ ገነት ስጋ ቤት ባለቤት አቶ ዘመኑ ገዱ ለዓመታት በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ቄራ ተመርቆ ሥራ በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸው ቄራው ፈጣን ፣ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀድሞ ቄራ አካባቢ የሚኖሩት ወይዘሮ ቤዛ አለሙ በበኩላቸው ለረዥም ዓመታት ካገለገለው ቄራ የሚወጣው የተበከለ ቆሻሻ ሽታ ለተለያየ በሽታ አጋልጧቸው እንደቆየ ጠቅሰው አዲሱ ቄራ ይህን ችግር የሚፈታልን ይሆናል ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራው የፌዴራልና ክልል ልዑካን በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሥራ የጀመሩትን ባለሃብቶችን የሥራ እንቅስቃሴ በወቅቱ በመመልከት አበረታተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም