የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት በኮሮና ቫይረስ ተያዙ

150

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ በኮሮና ቫይረስ ተያዙ። ከፕሬዚዳንቱ ጋር ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተጠቁሟል።

የአህጉሪቷ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ ተቋም ዛሬ በድረ ገጹ ፕሬዚዳንቱ  በቫይረሱ መያዛቸውን ይፋ አድርጓል።

ፕሬዚዳንቱ ከትናንት በስቲያ ግብጽ ሲገቡ መካከለኛ የጉንፋን ምልክቶች ማሳየታቸውንና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መመሪያን መሰረት አድርጎ ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱ ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ ፕሬዙዳንቱ ባረፉበት ሆቴል ለ14 ቀናት ራሳቸውን አግለው እንደሚቆዩም ጠቁሟል።

ከፕሬዚዳንቱ ጋር ባለፉት ሰባት ቀናት ግንኙነት የነበራቸው በተለይም  የካፍ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ፍጻሜን ለመመልከት ወደ ሞሮኮ ባቀኑበት ወቅት አብረዋቸው የነበሩ ሰዎች አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስዱ ተጠይቋል።

ፕሬዚዳንት ተቋሙን ለረጅም ዓመታት የመሩትን ኢሳ ሀያቱን በመተካት እንደ አውሮፓያን አቆጣጠር ከ2017 አንስቶ በመምራት ላይ ናቸው።

በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት ምርጫ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የስድሳ ዓመቱ ማዳጋስካራዊ የአገራቸውን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለ14 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት መርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም