ኢትዮጵያ የመምህራንን ቅን ህሊናና የሀገር ፍቅር ተጽዕኖ ፈጣሪነትን ትፈልጋለች - የትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ

79

ባህርዳር ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ የመምህራንን ቅን ህሊናና የሀገር ፍቅር ተጽዕኖ ፈጣሪነትን የምትሻበት ወቅት ላይ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መምህራን ቀን ምክንያት በማድረግ "መምህራን ቀውስ ለመቀልበስም ሆነ ለመጪው ጊዜ ብሩህነት ግንባር ቀደም ሚና አላቸው" በሚል መሪ  ሃሳብ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሚኒስትሩ በምክክር መድረኩ እንደተናገሩት  ዛሬ ላይ ሀገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የመምህራንን በጎ ህሊናና ቅን ሃሳብ ትሻለች።

መምህራን ያላቸውን እውቀት ለሀገር ሲያበረክቱ እንደኖሩ፣  ዛሬና ነገም ይህንኑ እንደሚያስቀጥሉ ጠቅሰው የሀገር ፍቅር ተጽዕኖ ፈጣሪነትም እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት የተተገበረው የትምህርት ስርዓት ውጤት ያስመዘገበ ቢሆንም ግብረ ገብነትንና መልካም ስነ ምግባርን  የተላበሰ ትውልድ በመፍጠር በኩል ውስንነት የታይበት ነበር ብለዋል።

ይህም ሀገሪቱ አሁን ላይ ለሚስተዋለው አለመግባባት፣ አለመከባበር፣ አለመፈቃቀርና አለመተሳሰብ  አሉታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።

ዓለም ከደረሰበት ጋር ሲወዳደር ከቴክኖሎጂና ኢኮኖሚ  ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያልሰጠ እንደነበር ያወሱት  ሚኒስትሩ በአዲሱ የትምህርት ስርዓት ለማካተት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

መምህራን የሰላም አምባሳደር ናችሁ፤ መምህራን ትውልድን የመቅረጽ ሙያ  ከብሄር፣ ፖለቲካና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ወገንተኝነት የጸዳ መሆን አለበት ብለዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን እንዳሉተ በመምህራን ላይ  የሚሰሩ ማናቸውም ተግባራት ከሀገር ግንባታ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑን ጠቁመው የሙያውን ልዕልና በመመለስ ወደ ከፍታ ለማድረስ ሁሉም በጋራ መስራት ይኖርበታል።

በሃገር ደረጃ ካለው አንድ ሚሊዮን 400ሺህ የመንግስት ሰራተኛ   50 በመቶው መምህራን በመሆናቸው በሙያቸው የሚኮሩ፣ ለትውልድ ቀረጻ ሌት ተቀን የሚተጉ መምህራንን ማፍራት ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከመጀመሪያ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ መምህራን ከመቼውም በበለጠ  ዜጎችን በማነጽ በኩል ከመምህራን እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

"በአባቶቻችን ብርቱ ትግል ኢትዮጵያ  በአንድ ወቅት የስልጣኔ ማማ ከፍታ ላይ ደርሳ ነበር" ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ናቸው።

በዓይን የሚታዩና በእጅ የሚዳሰሱ ለትውልድ የተረፉ ቅርሶችን ያወረሱን የጥንት አባቶችና እናቶች  ፈተናን በጥበብ ማለፍ ብቻ ሳይሆን የከፍታ ማማ ላይ ለመድረስ የነበራቸውን ራዕይ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"የአሁኑ ትውልድም መመዘን ያለበት ተግዳሮቶችን በጥበብ በማለፍ" ነው ያሉት ዶክተር ፍሬው  የትምህርት ስርዓቱ  በየጊዜው የሚለዋወጥ ሳይሆን በሃገር በቀል እውቀትንና ለጥበብ ዋጋ በሚሰጥ መልኩ ተቀርጾ መተግበር እንዳለበት ተናግረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ  በበኩላቸው የመምህርነት ሙያ ለአንድ አገር ግንባታ ምሰሶ ነው ብለዋል።

የትምህርት ዘርፉ ለሀገር እድገት የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት እንዲችል መምህራንና ሙያው  የሚገባውን ክብርና  ጥቅም እንዲያገኝ በጋራ መስራት እንደሚኖርበት ገልጸዋል።

በሃገር ደረጃም ሆነ በአማራ ክልል መምህራን የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ እንዳልነበር ጠቅሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመኖሪያ ቤት መስሮሪያ ቦታና ሌሎች ማበረታቻዎች መጀመራቸው ብሩህ ተስፋ የሚያመለክት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ ባንቲ "የመምህራን ቀን መከበር  መምህራንን የሚያበርታቱ መልክቶች ስለሚተላለፉበት ለሙያው እድገት ተጨማሪ አቅም  ይሆናል" ብለዋል።

የመምህራን ቀን ሲከበር የወቅቱን ሁኔታ ማለፍ የሚያስችሉ አበረታች ጽንሰ-ሃሳብ ባላቸው መሪ ቃሎች ስለሚታጀብ  እንደ ልደት በዓል ይቆጠራል ሲሉ ገልጸዋል።

በትምህርት ሚኒስቴርና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የምክክር መድረክ  የህዝብ ተወካዮች አባላት ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና ክልል የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም