በአመጋገብ ባህል ለውጥ ላይ እየሰራሁ ነው-የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት ተቋም

86
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2010 የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት ተቋም በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የአመጋገብ ባህል በጥራትና በዓይነት እንዲያድግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡ ተቋሙ ቀደም ባሉ አመታት  በህብረተሰቡ ለምግብነት የሚዘወተሩ እና አሁን እየተረሱ የመጡ ምግቦችን ዳግም አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጿል። ተቋሙ በአመጋገብ ስርሀት ላይ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሄዷል። ተቋሙ በሰጣቸው ስልጠና ቀድሞ ከነበረ የአመጋገብ ስርዓት በመለወጣቸው በልጆቻቸው ላይ ይደርስ ከነበረው የመቀንጨር ችግር መላቀቃቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ሞዴል ቤተሰቦች ምስክርነት ይሰጣሉ። አርሶ አደር  ታደሰ ንጋቱ እና ባለቤታቸው  ወይዘሮ አሰግድ ይመር የመጡት ከአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተው ለደሬ ወረዳ ነው። ጎጆ ቀልሰው ስድስት ልጆችን ማፍራታቸውን የሚገልጹት ቤተሰቦቹ ግብርና እና  የጓሮ አትክልት ልማት ደግሞ ኑሯቸውን የሚደጉሙበት ነው፡፡ ታዲያ በግብርና እና በጓሮ አትክልት የሚያገኟቸውን የምርት ውጤቶች ወደ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ ለአመጋገባቸው  ትኩረት ሰጥተው እንደማይጠቀሙባቸው ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአካባቢው 'ዘላቂ ልማት መካነ ጥናት' የሚባል ተቋም  የአመጋገብ ባህልን ማሳደግ እንዲሁም በቀላሉ የጓሮ አትክልቶችን አልምቶ መጠቀም በሚቻልበት ዘሪያ ድጋፍና ስልጠና ከሰጠ በኋላ የአመጋገብ ባህላቸው መቀየሩን ይናገራሉ፡፡ ቀደም ሲል የተወለዱ አምስት ልጆቻቸው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የእድገት መቀንጨር እንዳጋጠማቸው የሚናገሩት ወይዘሮ አሰግድ ይመር፤ አሁን ላይ ግን በአካባቢያቸው በተመደበ ባለሙያ ባገኙት ስልጠና ስድስተኛ ልጃቸውን የተመጣጠነ ምግብ እንድትመገብ እንዳስቻላት ይጠቅሳሉ፡፡ በተመሳሳይ ባለቤታቸው አርሶ አደር ታደሰ ንጋቱ ባገኙት የአመጋገብና የምግብ አሰራር ስልጠና የአመጋገብ ባህላቸው እንዲያድግ መቻሉን ነው የሚያብራሩት፡፡ አርሶ አደሮቹ በቀጣይም ተቋሙ ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠናና ድጋፉን ተደራሽ በማድረግ  ተጠቃሚ የሚያደርግበትን ስርዓት እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡ የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት ተቋም አስተባባሪ አቶ አለማየሁ አያሌው  በበኩላቸው ተቋሙ ባለፉት ሁለት አመታት  አዲስ አበባን ጨምሮ በተመረጡ የአማራ፣ አሮሚያ፣ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የአመጋገብ ባህል በጥራትና በአይነት እንዲያድግ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል ብለዋል፡፡ በተለይም ደግሞ በገጠሩ የአገሪቷ ተራራማ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የአመጋገብ ባህላቸውን በአይነትም ሆነ በጥራት እንዲያሳድጉ ተቋሙ ስልጠና እና ድጋፍ ሰጥቷል። በዚህም ቁጥራቸው ሃያ አምስት የሚሆኑ የግብርና፣ የጤና ባለሙያዎችንና መምህራኖችን አነስተኛ ድጋፍ በማድረግ በጥቅሉ 440 አባወራዎች አመጋገባቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚከሰተውን የእድገት መቀንጨር መቀነስ ተችሏል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በህብረተሰቡ ቀደም ባሉ አመታት ለምግብነት የሚዘወተሩ ጠቀሜታቸው ላቅ ያሉ ምግቦችን ዳግም አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን ነው አቶ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም  በአማራና ኦሮሚያ  ብሔራዊ ክልሎች በተመረጡ አካባቢዎች ከስምንት መቶ በላይ አባዎራዎችና እማወራዎችን የአመጋገብ ባህላቸውን በአይነትና በጥራት እንዲሁም በማምረት ሂደት እንዲያሳድጉ ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም