በአክሱም ለግብይትና አገልግሎት ደረሰኝ የመቀበል ልምድ ማነሱ የገቢ አሰባሰቡ ላይ ችግር ፈጥሯል

74
አክሱም ግንቦት 5/2010 ለገዙት እቃም ሆነ አገልግሎት ተገቢውን ደረሰኝ የመቀበል ልምድ አለመዳበር በገቢ አሰባሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን የአክሱም ከተማ ገቢዎች ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የግብር ህጉን በጣሰ መልኩ በሚንቀሳቀሱ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የከተማው ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ጽሕፈት ቤት ገልጿል። በከተማው የገቢዎች ልማት ጽሕፈት ቤት የገቢ ልማት ክትትል ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብርሃነ ገብረማርያም  እንደገለጹት በደረሰኝ የመቀበልና የመስጠት ስርአትና በህጉ ዙሪያ ያለውን ክፍተት ለመሙላት በየአመቱ ለንግዱ ማህበረሰብ ስልጠና ይሰጣል። ይሁን እንጂ ችግሩ በሚፈለገው መጠን እየተቃለለ ባለመሆኑ በተለይም ህጉን ተከትለው በማይሔዱት ላይ የተለያዩ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ይገኛሉ። ከተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ 435 ነጋዴዎች መካከል  ደረሰኝ የማይቆርጡ 122 ነጋዴዎች ላይ የማስጠንቀቂያ እርምጃ መወሰዱን ገልጸው የተለየ ድጋፍና ክትትል የሚያስፈልጋቸው 80 ነጋዴዎች ደግሞ ልዩ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል። ህብረተሰቡም ደረሰኝ የመጠየቅ ልምዱን በማዳበር ለዚህ የማይተባበሩ ነጋዴዎችን ደግሞ በማጋለጥ  ስራ እንዲተባበር ጠይቀዋል። የንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ መምህር ገብረመስቀል ተካ በበኩላቸው የግብር ህጉን በማያከብሩ ነጋዴዎች ላይ ከሚወሰደው እርምጃ ባለፈ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችም በቅንጅት እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል በዚህ አመት ያለ ፍቃድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 635 ነጋዴዎች የንግድ ፍቃድ ወስደው ህጋዊ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል። የአክሱም ከተማ ነዋሪ አቶ ማሙ በየነ እንደተናገሩት እርሳቸውን ጨምሮ ሸማቹ ማህበረሰብ ለገዛበትና ለተጠቀመበት  ደረሰኝ የመጠየቅና የመቀበል ባህል አልዳበረም፡፡ "አልፎ አልፎ ደረሰኝ የሚጠይቁ ሰዎች ከተገኙም ለማወራረጃ የሚጠቀሙበት እንጂ በደረሰኝ የመገበያየትን ጠቀሜታ ከመገንዘብ አይደለም" ብለዋል። በከተማው በሆቴል ንግድ የተሰማሩት አቶ ኪዳነ ትኩዕ በበኩላቸው ለንግድ ስራ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ሲንቀሳቀሱ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ ደረሰኝ የመስጠት ልምዱ አነሳ መሆኑን እንዳረጋገጡ ገልጸዋል። ይህም መንግስት ማግኘት የሚገባውን ገቢ የሚያሳጣ  መሆኑን በመጥቀስ  የግብር አሰተዳደራዊ  ስርአቱን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም