በአዲስ አበባ በ4 አደባባዮች ላይ የትራፊክ መብራት መገጠሙ የትራፊክ መጨናነቅን መቀነሱ ተገለጸ

141

አዲስ አበባ  ጥቅምት  18/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ አራት አደባባዮች ላይ የትራፊክ መብራት መገጠሙ የትራፊክ መጨናነቅን መቀነሱንና የእግረኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ማስቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የመንገድ ትራፊክ ኦፕሬሽን እና ደንብ ማስከበር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሰመረ ጀላሎ እንደገለጹት ባለፈው በጀት ዓመት በመዲናዋ የሚገኙ አራት አደባባዮች ወደ ትራፊክ መብራት ተቀይረው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

በመዲናዋ ከ70 በላይ የትራፊክ መብራቶች የሚገኙ ሲሆን መብራቶቹ የታለመላቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ አሽከርካሪዎችና እግረኞች የትራፊክ ህግን በማክበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

የከተማዋ የመሰረተ ልማት ግንባታና የኢንዱስትሪ ማእከልነት እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የተሽከርካሪ ቁጥር እና እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተለየም በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ በከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ በመስተዋሉ ኤጀንሲው የትራፊክ መጨናነቅ መንስኤዎችን በማጥናት የማሻሻያ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ከማሻሽያዎቹ መካከል አደባባዮችን ወደ ትራፊክ መብራት መቀየር አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በከተማዋ ከ60 በላይ አደባባዮች እንደሚገኙና በ2012 በጀት ዓመት ብቻ አራት አደባባዮች ወደ ትራፊክ መብራት ተቀይረው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አደባባዮቹን አፍርሶ መብራቶቹን ብቻ ተክሎ የመሄድ ሁኔታ እንደነበር ሀላፊው አስታውሰው ማሻሻያ የተደረገባቸው አደባባዮች ላይ ለእግረኞችም ትኩረት በመስጠት 20 ሺህ ካሬ ሜትር የሚጠጋ የእግረኛ መንገድ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

የትራፊክ መብራት ከአደባባይ በተሻለ እንደ ተሸከርካሪው መብዛትና ማነስ በትራፊክ መብራቱ ላይ የተለያዩ ሰዓቶች በመመደብ የትራፊክ እንቅስቃሴው አንዲሳለጥ ያስችላልም ብለዋል ፡፡

የአፍሪካ ህብረትና ጦር ሀሃሎች ስራቸው ተጠናቆ በትራፊክ መብራት የማስተናበር አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን የአየር ጤና እና የጎሮ አደባባይ የትራፊክ መብራቶቹ በሙከራ ሂደት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

ኤጀንሲው አደባባዮቹን ወደ ትራፊክ መብራት በሚቀይርበት ጊዜ በአካባቢው የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ችግሮችን በመለየት አመርቂ ስራዎችን መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በትራፊክ መብራቶቹ አካባቢ በቅርብ ርቀት የሚገኙ የህዝብ ትራንስፖርት መጫኛና ማውረጃ ስፍራዎች የትራፊክ መብራቶቹ የታለመላቸውን ዓላማ እንዳያሳኩ ከሚያደርጉ ችግሮች አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኤጀንሲው በቀጣይም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ 

ኤጀንሲው ቀደም ሲል ሰባት አደባባዮች አፍርሶ ወደ ትራፊክ መብራት የቀየረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 18 ማዞሪያ፣ ኢምፐሪያል እና ሳሪስ አቦ ይገኙበታል፡፡

አደባባዮቹ ፈርሰው የትራፊክ መብራት ከተገጠመላቸው በኋላ በአካባቢው የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅና ይደርስ የነበረውን የትራፊክ አደጋ በመቀነስ መቻሉም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም