የነብዩ ሙሀመድ መወሊድ በዓል ውሱን አማኞች በተገኙበት በታላቁ አንዋር መስጊድ ይከበራል

122

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18/2013 ( ኢዜአ) 1 ሺህ 495ኛው የነብዩ ሙሃመድ የመወሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጊድ ውሱን ዓማኞች በተገኙበት ነገ እንደሚከበር የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ነዋሪዎች የማእድ ማጋራት ተግባር ተከናውኗል፡፡ 

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አሊ መሃመድ ሺፋ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ሙሰሊሙ የነብዩ መሀመድን ልደት የሚያከብረው የእሳቸውን የደግነት ሥራዎች ተግባራዊ በማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ዓላማ በመነሳት 1 ሺህ 495ኛው የነብዩ ሙሀመድ ልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ከታላቁ የአንዋር መስጂድ ወጣት ጀምዓ ጋር በመተባበርና የተለያዩ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ዛሬ ለአቅመ ደካሞች ማዕድ ማጋራት ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

"ነብዩ ሙሃመድ ለዓለም እዝነትና ደግነትን ያስተማሩ እንደመሆናቸው እኛም ተከታዮቻቸው ለሌሎች ወገኖቻችን እዝነትን ደግነትን በማሳየት አርአያነታቸውን ልንከተል ይገባል" ብለዋል ሼህ አሊ መሃመድ፡፡

ምክር ቤቱ 1 ሺህ 495ኛው የልደት በዓልን በተለያዩ ደማቅ ስነስርኣቶች ለማክበር ቢያስብም በአገሪቱ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በዓሉን ከ5 ሺህ ያልበለጠ ሰው በሚታደምበት ለማክበር መገደዳቸውን ተናግረዋል።

ሰሞኑን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሕዳሴው ግድብን አስመልክተው ያስተላለፉትን መልዕከት ምክር ቤቱ በጽኑ እንደሚያወግዘውና የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን እንጂ የማንም እንዳልሆነ  ሼህ አሊ መሃመድ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር እድሪስ በበኩላቸው "የነብዩን የልደት በዓል ስናከብር በእንደዚህ ዐይነት ማዕድ የማጋራት በጎ ተግባር ሌሎችን በማሰብ መሆኑ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል" ብለዋል፡፡

የነብዩን መውሊድ በዓል ሲከበር ደግ ሥራዎቻቸውንና እዝነቶችን ተግባራዊ በማድረግ መሆን እንዳለበትም ነው ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ያስገነዘቡት።

በማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው በበኩላቸው፤ "ታላቁ ነብዩ ሙሀመድ እስልምና የሰላም ሃይማኖት መሆኑን ዓለም እንዲገነዘብ ዋጋ የከፈሉ መሪ ናቸው" ብለዋል፡፡

የሃይማኖቱ መሪዎች፣ አባቶች፣ ወጣቶችና የእምነቱ ተከታዮች የአዲስ አበባን ሰላም ለማስጠበቅ ሁሌም የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ይህን ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ያቀረቡት ኮሚሽነር ፍሰሀ፤ ሁሉም የእምነት ተቋማት ለሰላም አብረው የሚሰሩበት ምክር ቤት እየተጠናከረ እንደሚመጣ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም