6 የካንሰር ሕክምና መስጫ ተቋማት እየተገነቡ ነው- ጤና ሚኒስቴር

115

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18/2013 ( ኢዜአ) የካንሰር ሕክምና የሚሰጡ ስድስት የጤና ተቋማት ግንባታ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ። 

ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ወርን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ "ኅብረተሰቡ ስለ ጡት ካንሰር  ያለው ግንዛቤ  ሊያድግ  ይገባል"  ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሴቶች በየዓመቱ በጡት ካንሰር እንደሚያዙና በኢትዮጵያም በካንሰር ከሚያዙ ሰዎች መካከል ሲሶ የሚሆኑት የጡት ካንሰር ሕሙማን መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 የጡት ካንሰር ሕመም ግንባር ቀደም ገዳይ በሽታ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም አብዛኛው የጡት ካንሰር ሕሙማን ወደ ጤና ተቋማት ዘግይተው መሄዳቸው አንድ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

"ለዚህም ደግሞ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆንና በተለይ ለካንሰር ሕሙማን አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማት እጥረት ተጠቃሽ ናቸው" ብለዋል ዶከተር ሊያ ።

ይህንን ሁኔታ ለማሻሻልም ሚኒስቴሩ የጡት ካንሰር ሕክምናን ተደራሽነት ለማስፋት በ12 የክልል ሆስፒታሎች የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ሕክምናውን እንዲሰጡ መደረጉን ጠቁመዋል።

እነዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ ለጡት ካንሰር ህክምና የሚያስፈልገውን ጊዜ ከዚህ ቀደም ከነበረበት ስድስት ወር ወደ ሁለት ሳምንታት ዝቅ እንዲል ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ ክልሎችና  በአዲስ አበባ ተጨማሪ ስድስት የጡት ካንሰር ሕክምና የሚሰጡ ተቋማት በግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ከእነዚህ መካከል ሦስቱ በመጪዎቹ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩና ቀሪዎቹም በቅርቡ  እንደሚጠናቀቁ  ሚኒስትሯ  አመልክተዋል።

ሴቶችም ስለበሽታው መንስኤና አስከፊነት ያላቸውን ግንዛቤ በማጎልበት እራሳቸውን ለጡት ካንሰር ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች መጠበቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በተለይም ደግሞ ጡትን በእጅ በመዳሰስና በመመርመር ከበሽታው ራስን መጠበቅ እንደሚገባ ሚኒስትሯ መክረዋል።

የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር ወር “ጡትዎን በእጅዎ በመዳሰስና በመመርመር የጡት ካንሰርን ይከላከሉ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚከበረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም