የአሜሪካ መንግስትና የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና ተገቢ አይደለም - ዶክተር አረጋዊ በርሄ

72

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18/2013 ( ኢዜአ) የአሜሪካ መንግስትና የዓለም ባንክ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና ዓለም አቀፍ መርሆዎችን የጣሰና ኢ-ፍትሃዊ ነው ሲሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ተናገሩ።

ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አረጋዊ በርሄ “በግድቡ ዙሪያ የሚደረግ ጫና ለኢትዮጵያዊያን አንድነትና ጉልበት ይሆናል እንጂ የጎላ ተጽዕኖ አይኖረውም” ብለዋል።

ዶክተር አረጋዊ በርሄ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ የአሜሪካ መንግስት በዓለም ባንክ በኩል የሚያደርገው ጫና ኢ-ፍትሃዊና ዓለም አቀፍ መርሆዎችን የጣሰ ነው።

"የዓለም ባንክ በዋናነት በዓለም ዙሪያ የአገሮችን ዕድገት የሚያረጋግጡ ልማቶችን የመደገፍ መርህ ይዞ የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ድርጅት ቢሆንም ከግድቡ ጋር በተያያዘ ይህን መርህ በኢትዮጵያ ላይ አልተከተለም" ሲሉ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የአሜሪካ መንግስት ዓለም ባንክን በመጠቀም በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲያደርግ እንደሚታይም ተናግረዋል።

በተለይም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ካደረጓቸው ንግግሮችና ጫናዎች አንዳንዶቹ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፉ እንደሆኑም ጨምረው አመልክተዋል።

"አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባላት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍላጎት የተነሳ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ገሃድ የወጣ አድሎ እየፈፀመች ነው" በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

አሜሪካና የአሜሪካ ህዝብ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች ሲገጥሙ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከግድቡ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ ጫና መደረጉ መታረም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

"የግድቡ ግንባታ የተጀመረው የኢትዮጵያን ህዝብ በመተማመን እንጂ እነሱን በመተማመን አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በቅርቡ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የተናገሩትን ንግግር ተከትሎ በኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ከፍተኛ የአንድነትና የተነሳሽነት ስሜት መፈጠሩንም ዶክተር አረጋዊ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም