በደቡብ ክልል የመማር ማስተማር ስራ በዞን ከተሞች በይፋ ተጀመረ

52

ዲላ፣ ጥቅምት 18/2013 (ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ተቋርጦ የቆየው መደበኛ የመማር ማስተማር ስራ በደቡብ ክልል በሚገኙ የዞን ከተሞች በይፋ ተጀመረ። 

የደቡብ ክልል ሁለተኛው ዙር የዞን ከተሞች የትምህርት ማስጀመሪያ መረሃ ግብር በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ  ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲጀመር የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ እንደገለጹት በጌዴኦ 314 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ242 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው ወደ ትምህርት ገበታ ተመልሰዋል።

ከነዚህ ውስጥ 24 ሺህ 500 የሚሆኑ የስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በሁለተኛው ዙር ትምህርት ማስጀመሪያ መረሃ ግብር ትምህርት መጀመራቸውን አመላክተዋል።

በዞኑ ወረርሽኙን በመከላከል ትምህርት ለማስቀጠል 443 ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች፣ 3 ሺህ 203 የተማሪ መቀመጫ ወንበሮችና መሰል የመማሪያ ግብዓቶች እንዲሁም የመምህራን ቅጥር ተከናውኗል ብለዋል።

የትምህርቱን ስራ በመደገፍ የዞኑ ህብረተሰብ በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ  ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ትምህርት እንዲጀመር የተደረገው በትምህርት ሚንስቴር የተቀመጠውን የኮሮና መከላከል መስፈርት መሟላቱ በመረጋገጡ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ ናቸው።

ተማሪዎች የቅድመ ጥንቃቄ መመሪያዎችን በመተግበር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ወላጅ፣ መምህራንና ሌሎችም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሁሉም ስፍራዎች የሚታየው መዘናጋት በትምህርት ቤቶች እንዳይደገም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንዲደረግ  አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም