ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ መዘጋጀቱን አስታወቀ

97

ጎንደር፣ ጥቅምት 18/2013(ኢዜአ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2013 የትምህርት ዘመን ኮሮናን እየተከላከለ መደበኛ ተማሪዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን መሰረት ያደረገ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በማድረግ በመጀመሪያው ዙር 5 ሺ 400 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስመረቅ  ተሰናድቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ለኢዜአ እንደተናገሩት በሀገሪቱ የኮሮና ወረርሺኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በሽታውን በመከላከልና ለህሙማንም የህክምና እርዳታ በመስጠት ተቋሙ  ማህበራዊ ሀላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል።

በዘንድሮ የትምህርት ዘመንም በሽታውን በመከላከል የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር ተቋሙ በማቆያነት ሲያገለግሉ የቆዩ ህንጻዎችን የኬሚካል ርጭት በማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-ሙከራዎች ፣ ቤተ-መጻህፍቶችና ሌሎች ለተማሪዎች መገልገያ የሚውሉ ህንጻዎችም ጥገና እና የቀለም ቅብ ስራዎች እንደተደረገላቸው ጠቅሰዋል፡፡

በአንድ ክፍል ውስጥ ሊማሩ የሚገቡ ተማሪዎችን ጨምሮ በቤተ-መጻህፍት ፣ በቤተ-ሙከራዎችና በካፍቴሪያዎች ሊገለገሉ የሚገባቸውን የተማሪ ቁጥር በመወሰን ዝግጁ ተደርገዋል ብለዋል።

ተማሪዎች ሲገቡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚጠቀሙባቸውን ግብአቶች ከማሟላት አንጻር ሳኒታይዘርና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች በበቂ መጠን የማምረት ስራ መከናወኑንም ዶክተር አስራት አስረድተዋል፡፡

ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆኑና በቀላሉ በእግር ብቻ የሚሰሩ የእጅ መታጠቢያዎችን በዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ባለሙያዎች ዲዛይን በማድረግና በማምረት ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ለተማሪዎች ህብረትና ለተማሪ የሰላም ፎረም አደረጃጀቶች ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የስልጠና መመሪያ መሰናዳቱንም ገልጸዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ በተለያየ መጠን የተዘጋጁ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር በማምረት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስናከፋፍል ቆይተናል ያሉት በዩኒቨርሲቲው የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶክተር ደሴ ጥበበ ናቸው፡፡

ተማሪዎች የሚጠቀሙባቸው የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘሮች በበቂ መጠን እየተመረተ መሆኑን ጠቁመው፤ በትምህርት ክፍሉ ስር የሚገኙ ስድስት የኬሚስትሪ ቤተ-ሙከራዎችም የኮቪድ በሽታን ታሳቢ ባደረገ መንገድ መደራጀታቸውን አስታወቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የመካኒካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህር ሙሉቀን አዳነ በበኩላቸው የትምህርት ክፍሉ 150 የሚሆኑ ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆኑ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ መታጠቢያዎችን አዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

የእጅ መታጠቢያዎቹ በተማሪዎች ማደሪያና መማሪያ፣ በምግብ አዳራሾችና በዩንቨርሲቲው መግቢያ በሮች ጭምር እንዲቀመጡ በማድረግ ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም ተጨማሪ 150 እየተመረቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው 24 ሺህ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ሲኖሩት በትምህርት ዘመኑ የመጀመሪያው ዙር መርሃ ግብር  5 ሺ 400 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስመረቅ ተዘጋጅቷል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው ሀገር አቀፍ የተማሪዎች የቅበላ መርሃ ግብር መሰረት ተቋሙ ከጥቅምት 28 እስከ 30 የመጀመሪያውን ዙር ተማሪዎች በመቀበል ህዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም መደበኛ ትምህርት እንደሚጀመር ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም