ለፀረ-ሙስና ትግሉ ውጤታማነት የአመራር ቁርጠኝነት ያስፈልጋል- የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን

124

አርባምንጭ ጥቅምት 17/2013 (ኢዜአ ) ለፀረ-ሙስና ትግሉ ውጤታማነት የመንግስት አመራር አካላት ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ የፌዴራል ስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ሙስናን በቅንጅት መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ ከፌደራልና  ክልሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ የምክክር መድረክ ዛሬ አካሄዷል፡፡

የፌደራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ፀጋ አራጌ በመድረኩ እንደገለጹት ሙስና  ዕውቀት፣ ስልጣንና ገንዘብ ባላቸው አካላት የሚፈጸም ወንጀል ነው።

በመንግስት በኩል ሙስናን ሊከላከሉ የሚያስችሉ አደረጃጀቶችና አሠራሮችን በመዘርጋት  ለህብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ በመስጠት የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

የፀረ- ሙስና ትግሉ በኮሚሽኑ ተጀምሮ  የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከዐቃቤ ህግና ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ሲሰራ ቢቆይም  የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ አለመምጣቱን ተናግረዋል።

የብልጽግና ጉዞ ጠላት የሆነውን ሙስና ለመከላከልና በዚህ ላይ የሚደረገውን ትግል ውጤታማ መሆን እንዲችል  የመንግስት አመራር አካላት ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ በቀጣይ ሙስናን በመዋጋት የላቀ አስተዋጽኦ ካላቸው ዐቃቤ ህግና ፖሊስ ጋር የጀመረውን የቅንጅት ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ በበኩላቸው የፀረ-ሙስና ትግሉ በስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በኩል ብቻ መፈጸሙ ዘላቂ ለውጥ ሊመጣ አለመቻሉን ተናግረዋል።

በሙስና ወንጀል ድርጊት የተሳተፉ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ተቀናጅተን የምንሠራበት አግባብ ላይ የደረስን በመሆኑ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለዋል።

ሙስና ጥቂት ግለሰቦች በህዝብ ሀብት የሚበለጽጉበትና በአንፃሩ ህዝቡን ተጎጂ የሚያደርግ ወንጀል ነው ያሉት ደግሞ በሲዳማ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ስጦታ ወንጨፎ ናቸው።

ማንኛውም የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከሙስና ነጻና ስኬታማ እንዲሆን የሙስና ወንጀልን በመከላከል ዙሪያ ህዝብን ያሳተፉ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ይህንን ችግር ለመከላከል ከመገናኛ ብዙሃን፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ኃይማኖትና ሌሎችም አካላት ጋር አብረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መልካሙ ስሬ በበኩላቸው ሙስና በሀገሪቱ  ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት  ፍትህ በገንዘብ እየተገኘ በመሆኑ ሙስናን በመከላከሉ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ተቋማት በቅንጅት ለመስራት መስማማታቸው ችግሩን ለመቀነስ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናገረዋል።

ቋሚ ኮሚቴውም የተቋማትን አሠራር በመከታተልና በመቆጣጠር በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርም አስታውቀዋል።

በምክክር መድረኩ የፌደራልና አስሩ ክልሎች የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽነሮች ፣ዐቃቤ ህጎችና የፖሊስ ኮሚሽነሮች መሳተፋቸውን ሪፖርተራችን ከአርባምንጭ ዘገቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም