በሲዳማ ክልል የቡና ምርትና ግብይት ጥራት ተጠብቆ አርሶ አደሩ የተሻለ እንዲጠቀም ይሰራል- ርዕሰ መስተዳድሩ

63

ሀዋሳ ጥቅምት 17/2013 (ኢዜአ ) የቡና ምርትና ግብይት ጥራትና ህጋዊነቱን ጠብቆ አርሶ አደሩ የተሻለ እንዲጠቀም ለማደረግ እንደሚሰሩ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ  ቡና አምራች  ወረዳዎች የመስክ ምልከታ ባካሄዱበት ወቅት የቡና ልማቱን ዘመናዊና የተሻለ ለማድረግ በባለሙያ ታግዞ የተከናወነው ስራ የአርሶ አደሩ  ተጠቃሚነት ማደጉን እንዳዩ ተናግረዋል።

ለውጥ ያመጡ አርሶ አደሮችን ተሞክሮዎች ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

ከምርት ማሻሻሉ በተጓዳኝ  ጥራቱን ጠብቆ ለገበያ እንዲቀርብና አምራቹ አርሶ አደር በልፋቱ ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ የግብይት ሥርዐት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ገልፀው በዚህ ሂደት ውስጥ ተግዳሮት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

በተለይ እሸት ቡና ለመሰብሰብ ከተፈቀዱ ቦታዎች ውጭ የሚካሄዱ ትናንሽ ግብይት ስፍራዎች እንዲሁም የቡና ኮንትሮባንድ ንግድና ደላሎች የቡናን ጥራት በማጓደልም ሆነ ዋጋውን በማሳጣት የአምራቹን ተጠቃሚነት እንደሚጎዱት ጠቅሰዋል።፡

ይህንን ተግባር በሕግ አግባብ ለመከላከልና ከማሳ  ጀምሮ እስከ ማዕከላዊ ገበያ ድረስ ባለው ሰንሰለት ጥራትና ሕጋዊ ሂደትን ብቻ ተከትሎ እንዲከናወን ለዚህ ሥራ በተዋቀረ ግብረ-ኃይል አማካይነት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ምርት ዘመን የሲዳማ ቡና በዓለም አቀፍ መድረክ አንደኛ መውጣቱን ጠቁመው የአካባቢውን ቡና በይበልጥ ለዓለም ማስተዋወቅና በዚሁ ልክ ዋጋውን ማሳደግም ሌላው የትኩረት አቅጣጫቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው እየተከናወነ ባለው የቡና ልማት ሥራ የአርሶ አደሩ ምርት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ሆኖም  በጥቂት ሞዴል አርሶ አደሮች ብቻ እየተተገበረ ያለው የምርትና ምርታማነት ማሻሻያ ፓኬጅ ወደ ሁሉም አርሶ አደሮች መስፋፋት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በምርት ዕድገቱ ልክ ጥራቱን ጠብቆ ለገበያ እንዲቀርብ በማድረግ የአምራቹንም ሆነ የቡና አቅራቢዎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ደግሞ ሌላው ትኩረት የተሰጠው ተግባር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ዘንድሮ ከክልሉ 25 ሺህ 777 ቶን  ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱንና ከዚህም  89 በመቶው የታጠበ ቀሪው ያልታጠበ ለማመቻቸት  እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታው ማሳቸው ከተጎበኘ አርሶ አደሮች መካከል የወንሾ ወረዳ ነዋሪ ክፍሌ ላንቃሞ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት በቂ ምርት ባለማግኘታቸው ተስፋ ቆርጠው እንደነበር አውስተዋል።

ያረጁ ቡናዎችን በመንቀል በአንድ ሔክታር ላይ ሁሉንም የምርት ማሻሻያ ተግባራትን በመከወን ያለማሁት ቡና አሁን ላይ አጥጋቢ ውጤት እያሳየኝ ነው ብለዋል፡፡

ባመረቱት  ልክ በዋጋውም ተጠቃሚ መሆን እንደሚፈልጉም ጠቁመዋል።

በአለታ ወንዶ ወረዳ የሚገኘው የሆማቾ ዋኤኖ የቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ቢልጣ ቢፋቶ በበኩላቸው የማህበሩ አባል አርሶ አደሮች ጥራት ያለው ቡና ብቻ እንዲያቀርቡ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ማህበሩ ባለው የቡና መፈልፈያና ማጠቢያ ኢንዱስትሪ አምና  ጥራቱን የጠበቀ የታጠበ ቡና አዘጋጅቶ  ለማዕከላዊ ገበያ ካቀረበው ውስጥ  80 በመቶው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዘ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከዚህም 31 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ጠቅሰው  ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ለአባላቱ ባቀረቡት የቡና መጠን ልክ ትርፍ ማከፋፈሉን ገልጸዋል።

ዘንድሮ 90 በመቶ የሚሆነውን ቡና አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት እንደሚጥሩ አሰረድተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ከግብርና ዘርፍና ሌሎች አመራሮች ጋር  ያካሄዱት የመስክ ምልከታ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የቡና ልማት ሥራዎችንና ግብይት ለመገምገም እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም