በሐረሪ ለ542 ነጋዴዎች የግብር ፣ ቅጣትና ወለድ እዳ ተሰረዘ

75

ሀረር ጥቅምት 17 ቀን 2013(ኢዜአ) በሀረሪ ክልል በኮሮና ክስተት ምክንያት የተቀዛቀዘውን የንግድ እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ ለ542 ነጋዴዎች የግብር፣ የቅጣትና የወለድ እዳ ስረዛ ማድረጉን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ። 

ለነጋዴዎቹ የተደረገው ምህረት ከ193 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ተነግሯል ።

የሀረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰሚራ ዩሱፍ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ለነጋዴዎቹ ምህረቱ የተደረገው የክልሉ ካቢኔ ባሳለፈው ወሳኔ መሰረት ነው።

በወሳኔው መሰረት ለ214 ነጋዴዎች ከ1997 እስከ 2008 ዓ.ም የነበረባቸው የውዝፍ የግብር እዳ ስረዛ መደረጉን ተናግረዋል ።

እንዲሁም ለ328 ነጋዴዎች ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም የነበረባቸው የቅጣትና ወለድ ሙሉ ለሙሉ መሰረዙን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ ለ542 ግብር ከፋዮች ከ193 ሚሊየን ብር በላይ የግብር፣ የወለድና የቅጣት እዳ ስረዛ መደረጉን አስታውቀዋል ።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ተፅዕኖ ምክንያት የንግዱ ማህበረሰብ ከእንቅስቃሴው እንዳይስተጓጎል ለመደገፍ  ምሀረቱ መደረጉን አመላክተዋል።

በንግዱ ዘርፈ ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎች ከስራ እንዳይቀነሱ፣ ነጋዴዎች በቤት ኪራይ ሳቢያ የንግድ ስራቸውን እንዳያቋርጡና ኮሮናን በመከላከል ሂደት የባለሀብቱን ተሳትፎ ለማበረታታት ምህረቱ መደረጉን አስታውቀዋል ።

በሆቴል ዘርፈ ስራ የተሰማሩ አቶ ደሳለኝ አስፋው በሰጡት አሰተያየት የኮሮና ቫይረስ ክስተት በንግድ ስራቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል ።

"የተደረገልኝ  የቅጣትና ውዝፍ ክፍያ ስረዛ ስራየን በንቃት እንድንሰራ አነሳስቶኛል" ብለዋል ።

"የኮሮና ክስተት በስራየ ላይ ባሳደረው ተጽዕኖ የሰራተኛ ደመወዝ መክፈል አቅቶኝ ነበር" ያሉት ደግሞ ሌላው በሆቴል ስራ የሚተዳደሩ አቶ ሐይሌ ዋጂ ናቸው።

"መንግስት ያነሳልን የግብር ውዝፍና ቅጣት ክፍያ የስራ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው " ብለዋል ።

በሐረሪ ክልል ከ13ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች እንደሚገኙ ታውቋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም