መገናኛ ብዙሃን ሙስናን ለመከላከል ቋሚ መርሃ ግብር ቀርፀው እንዲሰሩ ተጠየቀ

137

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል መገናኛ ብዙሃን ቋሚ መርሃ ግብር ቀርጸው እንዲሰሩ ተጠየቀ።

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ የጸረ-ሙስና ማህበር ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ከሲቪል ማህበራት ጋር ሙስናን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው።

በኢትዮጵያ ብልሹ አሰራሮችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመከላከል መገናኛ ብዙሃን ማህበረሰብን በማንቃት ሚናቸው የጎላ ነው ተብሏል።

የህግና የሚዲያ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ጎሹ መገናኛ ብዙሃን ሙስናን በመታገል ያላቸው ተግባርና ሚና ላይ ያተኮረ ጹህፍ አቅርበዋል።

መገናኛ ብዙሃን በጸረ-ሙስና ትግል ተዋናይ ከመሆን ባለፈ ማህበረሰብን በማንቃትና ንቅናቄ በመፍጠር ያላቸውን ሚና በጹህፋቸው አንስተዋል።

በአለም አቀፍና አገር አቀፍ ደረጃ የአገርና ህዝብ ሃብት በመመዝበር የሚፈጸሙ ውስብስብ የሙስና ወንጀሎችን በማጋለጥ መገናኛ ብዙሃን አቅም እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ሙስና አስጊ ችግር እየሆነ ቢመጣም መገናኛ ብዙሃን በሚፈለገው መጠን ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው አለመስራታቸውን አንስተዋል።

መረጃ ያለማግኘት፣ የጋዜጠኞች የክህሎት ክፍተት፣ ህዝባዊ አመኔታ ያለማግኘት፣ የአስፈጻሚ አካላት ጣልቃ ገብነትና ሌሎች ችግሮች በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሰሩ ካደረጓቸው ውስጥ ዘርዝረዋል።

ከተወሰኑ የህትመትና ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ውጭ አብዛኞቹ በሙስና ላይ የሚያተኩር ቋሚ መርሃ ግብር ቀርፀው ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው እየሰሩ አይደለም ብለዋል።

በመሆኑም የምርመራ ዘገባዎችን በማጠናከር፣ሙሰኞችን በማጋለጥ፣ የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ትምህርት በመስጠት መልካም አስተዳደርና ሙስና ላይ ያተኮሩ ተከታታይ ስራዎችን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም የጋዜጠኞችን ክህሎት በማጎልበት፣ የስራ አካባቢን ምቹ በማድረግ፣ ነጻና ገለልተኛ በመሆን እንዲሰሩ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት የህግ ባለሙያው።

መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት ማድረግ፣ የአስፈጻሚ አካላት ጣልቃ ገብነትን ማስቀረት፣ መገናኛ ብዙሃን ይፋ በሚያደርጓቸው መረጃዎች ላይ ተመስርቶ እርምጃ መውሰድም በመንግስት በኩል የሚጠበቅ ስራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ዋና ዳሬክተር አቶ ሳሙኤል ካሳሁን እንዳሉት በኢትዮጵያ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ሙስናን ለመከላከል የሰጡትን ትኩረት ለማወቅ ተቋማቸው ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አንድ ተቋም ብቻ ቋሚ መርሃ ግብር እንዳለው ተመልክቷል።

የአገርና የህዝብ ሃብት እንዳይመዘበር መገናኛ ብዙሃን አስፈጻሚ አካላትን በመጠየቅና  በትምህርታዊ መርሃ ግብሮች ማህበረሰብን በማንቃት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በዛሬ ውይይት ጋዜጠኞች ሙስናን ለማጋለጥ በሚሰሯቸው ዘገባዎች በተግባር እያጋጠማቸው ያሉ ችግሮችን አንስተው መክረዋል።

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ከመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞችና ሲቪል ማህበራት ጋር የጀመረውን ውይይት በቀጣይም ከመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች ጋር እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ በ2002 ዓ.ም የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ አገር በቀል ተቋም ሲሆን በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚስተዋለውን የሙስና ወንጀል በመከላከል ሲሰራ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም