ለእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኑ ተመርጠው ከነበሩት ተጨዋቾች መካከል አስሩ ተቀነሱ

46

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17/2013 ( ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለብሄራዊ ቡድኑ መርጠዋቸው ከነበሩት ተጨዋቾች መካከል አስሩን መቀነሳቸውን አስታወቁ።

በካሜሮን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የሚደረገው የማጣሪያ ጨዋታ በህዳር ወር 2013 ዓ.ም ዳግም ይጀመራል።

የኢትዮጵያ ወንዶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከኒጀር ጋር ላለባቸው የደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታ ከሶስት ሳምንት በፊት ለተጫዋቾች ጥሪ አድርገው ነበር።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በካፍ አካዳሚ ልምምዳቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።

ዋልያዎቹ ከኒጀር ጋር ላለባቸው ጨዋታ ይረዳቸው ዘንድ ጥቅምት 12 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም ከዛምቢያ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ከቀረበላቸው ተጫዋቾች መካከል 10 ተጫዋቾችን በመቀነስ 26 ተጫዋቾችን ማሳወቃቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

በግብጽ ምስር ኤል ማካሳ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ የፊታችን አርብ ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚቀላቀልም ተገልጿል።

በቀጣይ አራት ተጫዋቾች ተቀንሰው 23 ተጫዋቾች ወደ ኒጀር እንደሚሄዱ ተጠቁሟል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከኒጀር አቻው ጋር የሚያደርገው የመልስ ጨዋታ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይካሄዳል።

ዋልያዎቹ ከዛምቢያ ጋር ባደረጓቸው ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች 3 ለ 1 እና 3 ለ 2 በሆነ ውጤት መሸነፋቸው ይታወሳል።


ውበቱ አባተ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ለማሠልጠን የሁለት ዓመት ውል መፈረማቸው የሚታወስ ሲሆን በውሉ መሠረት ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ የማሳለፍ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ዋልያዎቹ በማጣሪያው በሚገኙበት ምድብ 11 የኮትዲቯር አቻውን አሸንፎ በማዳጋስካር ተሸንፎ በ3 ነጥብ ከማዳጋስካር በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ወንዶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም ከኮትዲቯርና ማዳጋስካር ጋር ቀሪ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቹን ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም