የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን አገራት መጻኢ ዕድል ብሩህ ያደርገዋል...የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች

64
አርባ ምንጭ ሐምሌ 9/2010 የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን አገራት መጻኢ ዕድል ብሩህ እንደሚያደርገው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ያዕቆብ ጌጃ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ የኢትዮጵያን ምድር ይረግጣሉ ብለው  ለአንድም ቀን አስበው እንደማያቁ ተናግረው በአሁኑ ወቅት በአገራቱ መካከል ሰላም መውረዱ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ከሃያ ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው "የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ በሁለት አገራት የሚኖሩ አንድ ህዝብ ናቸው፤ የተለያዩ ህዝቦች አድርገው የሚያስቡ ካሉ ሞኝ ናቸው" ማለታቸው የተለየ ስሜት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡ አገራቱ ቅሬታቸውን ትተው ወደሰላም መምጣታቸው በቀጣይ ሁለቱም በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ መስኮች አብሮ ለማደግ አዲስ ምዕራፍ ይከፍትላቸዋል የሚል እምነት እንዳደረባቸውም ተናግረዋል፡፡ "በተለያየ ጊዜ ሲነገር እንደነበረው የኤርትራው ፕሬዝዳንት አምባገነን ሳይሆኑ ሰው አክባሪና አብሮ መበልጸግን የሚወዱ መሪ መሆናቸውን አሁን በተፈጠረው የኢትዮጵያና ኤርትራ መልካም ግንኙነት መረዳት ችያለሁ" ያሉት ደግሞ አቶ እንጃ ገልሲሞ ናቸው፡፡ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የዶክተር አብይ አህመድን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደሰላም መምጣታቸው ለቀጠናው አገራት ሰላምና አብሮ መበልጸግ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ከመሆኑ በተጨማሪ የአገራቱን መጻኢ ዕድል ብሩህ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ንግስት ተፈራ ሌላዋ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ "የኢትዮጵያና ኤርትራ  ግንኙነት ተራርቀው የነበሩ የአንድ ቤተሰብ አባላትና ወንድማማች ህዝቦችን እርስ በርስ የሚያገናኝ ታሪካዊ ክስተት ነው" ብለዋል፡፡ ከሁለት አስርት ዓመታት ቅራኔ በኋላ የተፈጠረው የሁለቱ አገራት ወዳጅነት "በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በህዝቦች መካከል ልዩነት ለመፍጠር በፀብ አጫሪነት ለተሰማሩ ግለሰቦች ትምህርት ይሰጣል" ሲሉ አመልክተዋል፡፡ መንግስት የህገዝቦችን አንድነት ለማደፍረስ በሚቃጡ ኃይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ የጠቆሙት ወይዘሮ ንግስት፣ በአካባቢያቸው የጸጥታ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን በመጠቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል፡፡ የአዲስ አበባና የሃዋሳ ከተማ ህዝብ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከልብ የማይጠፋ ፍቅርና አክብሮት ማሳየታቸው እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደግሞ አቶ ዓለማየሁ ባሳ  የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ሁለቱ አገራት በደረሱት ስምምነት መሰረት ዛሬ በአዲስ አበባ የኤርትራ ኤምባሲ መከፈቱ ግንኙነታቸውን ለማቀላጠፍ እንደሚያግዝ ገልጸው፣ የአገራቱ ወደሰላም መምጣት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከርና በጋራ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ መጠናከር እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም