አንጋፋው ሠዓሊ የክብር ዶክተር ሎሬት ለማ ጉያ አረፉ

288

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2013 (ኢዜአ) አንጋፋው ሠዓሊ የክብር ዶክተር ሎሬት ለማ ጉያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

የቀብር ስነ-ስርዓታቸው በመጪው ሐሙስ በትውልድ ቦታቸው ይፈጸማል።

አንጋፋው ሠዓሊ ለማ ጉያ ዛሬ  ከቀኑ በ6 ሠዓት በቢሾፍቱ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በ92 ዓመታቸው ሕይወታቸው ማለፉን የሠዓሊው ወንድም አሰፋ ጉያ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሠዓሊ ለማ ጉያ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።

የአንጋፋው ሠዓሊ ለማ ጉያ የቀብር ስነ ስርዓት ሐሙስ ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ.ም በትውልድ ቦታቸው በቢሾፍቱ ከተማ በምትገኘው ደሎ ቀበሌ ይከናወናል ብለዋል።

የቀብር ስነ ስርዓታቸውን የሚያስፈጽም ኮሚቴ የተቋቋመ በመሆኑ ዝርዝር የቀብር አፈጻጻም ጉዳዮችን የሚገለፅ እንደሆነም ተናግረዋል።

አንጋፋው ሠዓሊ ለማ ጉያ ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ከአባታቸው አቶ ጉያ ገመዳና ከእናታቸው ወይዘሮ ማሬ ጎበና በቢሾፍቱ ከተማ በምትገኘው ደሎ ቀበሌ ነው የተወለዱት።

በልጅነታቸው የእናታቸውን የወይዘሮ ማሬ ጎበናን የዕደ ጥበብ ሙያ በተለይም ከመገልገያ መሳሪያ የሸክላ ውጤቶች በማየት የተለያዩ የቅርጻ ቅርጽ ስራዎችን ይሰሩ እንደነበር የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

አንጋፋው ሠዓሊ በታዳጊነታቸው የሚሰሯቸው የእንስሳት፣ የሰው፣ የመሳሪያና የቁሳቁስ ቅርጾች የትውልድ አካባቢያቸውን ነዋሪዎች ያስገርሙ እንደነበርና ስራዎቻቸው ወደ ዘመናዊ ትምህርት እንዲገቡ አመቺ አጋጣሚ እንደፈጠሩላቸው ይነገራል።

በ15 ዓመታቸው ትምህርት የጀመሩት ሠዓሊው እስከ ሰባተኛ ክፍል ከተወለዱበት ደሎ ቀበሌ 10 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው አፄ ልብነ ድንግል ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

ሠዓሊ ለማ ጉያ እስከ ሰባተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ባላቸው ጉጉት ወደ መምህራን ተቋም ቢገቡም ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤተሰባቸው ተመለሱ።

ሠዓሊው ወደ ስነ ጥበብ ዘርፉ ዘልቀው ለመግባት በየሳምንቱ መጨረሻ ወደ ቢሾፍቱ የሚመጡትን አፄ ኃይለ ስላሴን የሚያማልል የጥበብ ስራ ሰርተው የአጃቢዎችና የኘሮቶኮል ሹሞችን ክልከላ በዘዴ በመወጣት የአውሮፕላን ሞዴል ስራቸውን ማሳየትን እቅዳቸው አደረጉ።

የሠዓሊ ለማ የቅርጽ ጥበብ በንጉሱ አድናቆትን በማግኘቱ መማር የሚፈልጉትን በጠየቁት መሰረት አየር ኃይል ገብተው እንዲማሩ ትዕዛዝ ተላለፈላቸው።

ወታደራዊ ስልጠናቸውን ወስደውና በወጣት ዕጩ የፖሊስ ኃይል ሰልጣኝ /ካዴት/ ተመርቀው ወደ አስመራ ከተማ በመሄድ በአየር ኃይል መምህርነት ማገልገሉን ጀመሩ።

በከፍተኛ ውጤት የተመረቀው የያኔው ወጣቱ የአየር ኃይል ቴክኒሻን ለማ ጉያ ከአፄ ኃይለስላሴ የስዕል መሳሪያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ለማ ጉያ ከሰለጠኑበት የአየር ኃይል ሙያ በተጓዳኝ የስነ-ጥበብ ሙያቸውን ሳይዘነጉ በአስመራ የጣልያኖች የስዕል ትምህርት ቤት ከደመወዛቸው እየከፈሉ በመማር ሙያቸውን አዳብረዋል።

በተለይም የቁም ስዕል /ፖትሬት/ መልክዓ ምድርና ቁሳቁስን በመጠቀም የሚሰራ ስዕል አሰራር  በመማር በተፈጥሮ የታደሉትን እውቀት ማዳበር እንደቻሉ የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።

በወታደር ቤት እምብዛም የሲቪል ጉዳዮች ባልተለመደበት ሁኔታ የስዕል አውደ ርዕዮችን በማቅረብ በአንድ በኩል በወታደራዊ ትምህርቱ የተሰጣቸውን ግዳጅ እየተወጡ በሌላ በኩል የኪነ-ጥበብ ፍቅራቸውን ሠርተው በማሳየትና ለጥበብ ቀናኢነታቸውን እንዳሳዩም ይነገራል።

የ11 ዓመት የአየር ኃይል ዘመናቸውን አጠናቀው ወደ ምድባቸው ደብረ ዘይት ቢመለሱም በኢትዮጵያ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት በተለይም ከ1955 ዓ.ም የታህሳስ ግርግርና የሠራዊቱ መከፋፈል ጋር በሚስሏቸው ስዕሎች ትርጉም እየተላበሰ ጎሸም ይደረጉ እንደነበርም ይነገራል።

ከተለያዩ የውጭ አገራት ዜጐች ከሚበረከቱላቸው የስዕል መጽሐፎች ለኢትዮጵያዊያን በሚስማማ መልኩ በኢትዮጵያ ታሪክ በዘርፉ የመጀመሪያ የሆነችው ስዕል ያለ አስተማሪ መፅሐፍ ትርጉም በትምህርት ሚኒስቴር ወጪ ታትሞ በመላ አገሪቷ በትምህርት ቤቶች እንዲሰራጭ አድርገዋል።

ሠዓሊ ለማ ጉያ በኢትዮጵያ የፖስተርና የህትመት ቴክኖሎጂዎች ባልዳበሩበት ወቅት የኢትዮጵያን ብሔሮችና ብሔረሰቦች የአለባበስና የአኗኗር ዘይቤ የሚገልፁ በተለይም የኦሮሞን ህዝብ ትውፊት የሚያጎሉ ስዕሎችን በመሳልና በማተም ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪካዊ አሻራቸውን እንዳስቀመጡ ይነገርላቸዋል።

ከ10 ሺህ በላይ ስዕሎችን በፍየል ቆዳ ላይ በመሳል አድናቆትን ያተረፉት አንጋፋው ሠዓሊ በተፈጥሯዊ አሳሳል ካበረከቷቸው ስራዎች መካከል "የሸክላ ገበያ" እና "የደንከል ልጃገረድ" በዋናነት ይጠቀሳሉ።

አንጋፋው ሠዓሊ ለማ ጉያ በቢሾፍቱ ከቤተሰቦቻው ጋር በመሆን "የአፍሪካ ሙዚየም" በሚል ባሰሩት የጥበብ ማዕከል ስራዎቻቸውን ሲያስጎበኙ ቆይተዋል።

በአፍሪካ ኅብረት ያገለገሉ ፀሐፊዎችን፣ በኦሮሚያ የባህል ማዕከል የኦሮሚያ ክልል ኘሬዚዳንቶችንና የኦሮሞ ባህልና ትውፊትን የሚያሳዩ የቆዳ ላይ ስዕሎችንም አበርክተዋል።

ሠዓሊው በጥበብ ስራዎቻቸው በሰሜን አሜሪካ የውስጥ ቅርስ ማኅበር ተሸላሚ የሆኑ ሲሆን የጅማ ዩኒቨርሲቲ በ2007 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል።

ዕድሜውያቸውን ሙሉ ለጥበብ የሰጡ አገር ወዳድና ባህል አዋቂ እንደሆኑ ብዙዎች የሚመሰክሩላቸው አንጋፋዊ ሠዓሊ ለማ ጉያ ምንም አይነት መደበኛ ትምህርት ሳይኖራቸው የተፈጥሮ ጥበባቸውን በማዳበር የጥበብ ተምሳሌት እንደሆኑም ይገለጻል።

ለ56 ዓመታት አብረዋቸው ከኖሩት የትዳር አጋራቸው ወይዘሮ አስቴር በቀለ ሶስት ሴቶችና ሁለት ወንዶች ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ስምንት የልጅ ልጆችንም አይተዋል።

አምስቱም ልጆቻቸው በስነ ጥበብ ሙያ ውስጥም ይገኛሉ።

ማስታወሻ- የሕይወት ታሪካቸው የተገኘው ሠዓሊ ለማ ጉያ ሰኔ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሲያገኙ ከተነበበው ግለታሪካቸውና ከወንድማቸው ከደራሲ አሰፋ ጉያ ጋር ከተደረገ ቃለመጠይቅ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም