በጣና ሀይቅ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም የማስወገድ ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል

68

ባህርዳር ጥቅምት 16/2013 (ኢዜአ) በጣና ሀይቅ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም የማስወገድ ብሄራዊ ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጣና ሀይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ። 

ኤጀንሲው እምቦጭን በማስወገድ የተከናወኑ ተግባራት፣ የነበሩ ጥንካሬዎች ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አያሌው ወንዴ በዚሁ መግለጫቸው  ለአንድ ወር በሚቆየው ብሄራዊ ዘመቻ እምቦጭን የማስወገድ ተግባሩ በነቃ የህብረተሰብ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ባለፈው ሳምንት በሁለት ቀበሌዎች የተጀመረው ዘመቻም አድማሱን በማስፋት እስከባለፈው አርብ ድረስ ወደ 26 ቀበሌዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት 60ሺህ ህዝብ ለማሳተፍ ታቅዶ በተደረገ ጥረት የዝግጅት ምዕራፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከ30ሺህ በላይ ህዝብ ማሳተፍ መቻሉን ጠቁመው ከዛሬ ጀምሮ የተሳታፊ ቁጥሩ እንደሚጨምር ይጠበቃል ብለዋል።

በተለዩ በ43 የማስወገጃ ጣቢያዎች ላይ የማረም፣ የመሰብሰና የማከማቸት ስራ በማከናወን  ለማቃጠል ዝግጁ መደረጉን አመልክተዋል።

በተለይም አርሶ አደሩን ተሳትፎ ለማሳደግ የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን በመጠቀም እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ወደ ስራያልገቡ አካባቢዎችም ዛሬ ሙሉ በሙሉ ወደ  ማስወገድ ተግባሩ ገብተዋል ብለዋል።

በእምቦጭ ማስወገድ ስራው ያጋጠመውን የመዳረሻ መንገድ፣ የተሽከርካሪ፣ የንጽህና መጠበቂያ ፣ የቅባት፣ የአልባሳትና የህክምና አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል  ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሰው ኃይል ከሚደረገው የእምቦጭ ማስወገድ ባሻገር 6  ማሽኖችና 10 ትራክተሮችን በማሰማራት  የተቀናጀ የማስወገድ ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በብሄራዊ ደረጃ የተዋቀረው እምቦጭን የማስወገድ የቴክኒካል ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ዘሪሁን በበኩላቸው እምቦጭን በማስወገድ ዘመቻው የአካባቢው አርሶ አደር በነቂስ እየወጣ ያሳየው ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የወጣውንና የቀረውን የእምቦጭ አረም በትክክለኛ ማስረጃ አስደግፎ ለመግለጽ የሚያስችሉ  ሶስት "ድሮኖች" ከኢንሳ በመምጣታቸው በቀጣይ ሳምንት ወደ ስራ እንደሚገቡ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም