የቱሪዝም ዘርፉን ወደ ነበረበት ለመመለስ የፕሮቶኮል መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ተገባ

61

ባህርዳር ጥቅምት 16/2013 (ኢዜአ) በኮሮና ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ ወደ ነበረበት ለመመለስ የፕሮቶኮል መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ገለጹ።

በክልሉ፣ ባህር ዳርና አካባቢው  የቱሪዝም እንቅስቅሴውን በአዲስ መልክ የማስጀመር  መረሃ-ግብር ትናንት  በጢስ አባይ ፏፏቴ ተካሂዷል።

ሚኒስትሯ በመረሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው እንዳሉት በወረርሽኙ ሳቢያ የዓለም የቱሪዝም ሴክተር ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

በኢትዮጵያም  የቱሪዝም ዘርፉ በእጅጉ በመቀዛቀዙ በቱሪስት መዳረሻዎች የሚገኙ ሆቴሎች፣ አስጎብኝዎችና  ሌሎችም የዘርፉ ተዋናዮች ከስራ ውጭ ሆነው መቆየታቸውን አውስተዋል።

አሁን ላይ ኮሮናን እየተከላከሉ ተወዳዳሪ የሆነ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለመገንባት የሚያስችል ሀገራዊ የፕሮቶኮል መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

በመመሪያው  መሰረት  ለጎንደር፣ ደባርቅ፣ ላልይበላና  ባህር ዳርና አካባቢዎ ለሚገኙ 663 በቱሪዝም ሰንሰለቱ ለሚገኙ ተዋናኞች   ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

ከባህር ዳርና አካባቢዋ የቱሪዝም መዳረሻዎች በተጨማሪ በጎንደርና ደባርቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንደ አዲስ ስራ የማስጀመር መረሃ ግብር መከናወኑን ተናግረዋል።

"ለጉብኝት የመጣ እንግዳ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ ታመመ የሚባል ዜና መሰማት የለበትም፤  እራስን ከኮሮና ቫይረስ እየተከላከሉ ለጎብኝዎችም አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የሀገራችን ገጽታ መገንባት አስፈላጊ ነው "ብለዋል።

የፕሮቶኮል መመሪያውን በተሟላ መልኩ እየተገበረ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊነት መስተንግዶ ተቀብሎ የሚሸኝ የቱሪዝም ተዋናይ የማበረታቻ እውቅና እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።

የቱሪዝም ዘርፍ ከሰዎች እንቅስቃሴ ጋር  የተቆራኘ በመሆኑ ቫይረሱ ዘርፉን  ክፉኛ እንደጎዳው የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር  ሙሉቀን አዳነ ናቸው።

"እንቅስቃሴው እንደገና ተጀምሮ ከዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲገኝም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል።

የዘርፉ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት እስኪመለስ ድረስ ብዙ ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ዶክተር ሙሉቀን   የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከቫይረሱ የጸዳ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህም የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ከወረርሽኙ ተጠብቀው በጤና እንዲመለሱ የሚያስችል መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የባህር ዳርና አካባቢ  አስጎብኝዎች ማህበር አባል ወጣት የሽዋስ ምህረት  በሰጠው አስተያየት የኮሮና ቫይረስ በቱሪዝም ዘርፍ በመሰማራት ኑሮውን ለሚመራ ህብረተሰብ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጿል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አማካኝነት የማስጀመሪያ ሥነ- ሥርዓት ተካሂዶ ይፋ መሆኑ የአካባቢውን  የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ያስችለዋል ብሏል።

በሚኒስቴሩ የተሰጠው ስልጠናም ራሳቸውን ከቫይረሱ በመከላከል ጎብኝዎችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው ግንዛቤያቸውን እንዳሳደገላቸውም ተናግሯል።

ቱሪዝምን እንደ አዲስ በማስጀምር መረሃ-ግብሩ ላይ የፌዴራልና በክልሉ የሚገኙ የዘርፉ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም