ባለስልጣኑ በሩብ ዓመቱ ከተለያዩ አገልግሎቶች ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰብስቧል

94

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን በ2013 ሩብ ዓመት ከተለያዩ አገልግሎቶች ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡ 

ሁለት አዳዲስ የቴሌኮም ኩባንዎችን ወደ ስራ ለማስገባት በተከናወነ ስራ 12 ዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎች የፍላጎት ማሳያ መግለጫ ምላሽ መስጠታቸውንም ገልጿል።

ባለስልጣኑ የ2013 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙንና የቴሌኮም ሪፎርም ሂደቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ባልቻ ሪባ እንዳሉት በሩብ ዓመቱ ከፈቃድ መስጠትና እድሳት እንዲሁም የብቃት ማረጋገጫ አገልግሎቶች 25 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል።

"የውስጥና የውጭ የቴሌኮም ኬብል ስራ፣ ማዞሪያ፣ የመሳሪያ ተከላ፣ ጥገናና የተጨማሪ አገልግሎት ስራ 302 አዳዲስ ፈቃዶች ተሰጥተዋል፤ ነባር 258 ፈቃዶችም ታድሰዋል" ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ለ28 አዳዲስ የፍሪኩዌንሲ እና ለ46 ነባር ፈቃዶችም የእድሳት አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

ለ99 የሬዴዮ መገናኛ መሣሪያዎችና ለአንድ የቪሳት መሣሪያ መጠቀሚያ ፈቃድ መሰጠቱንም አመልክተዋል። "አራት ነባር የቪሳት መሣሪያዎች ፈቃድ እድሳትም ተከናውኗል" ብለዋል።

ለ15 የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ አምስት የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ፈቃድ መታደሱንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

የቴሌኮም ዘርፉን ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ 18 መመሪያዎች መዘጋጀታቸውንም አቶ ባልቻ ተናግረዋል።

ለሁለት አዳዲስ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፈቃድ መስጠት የሚያስችል አዲስ የሬጉላቶሪ ማዕቀፍና ስትራቴጂያዊ መርህ ስለመዘጋጀቱም ጠቅሰዋል።

ሁለት አዳዲስ የቴሌኮም ኩባንዎችን ወደ ስራ ለማስገባት በተከናወነ የስራ ሂደትም 12 ዓለምዓቀፍ ኩባንያዎች የፍላጎት መግለጫ መጠየቂያ ምላሽ መስጠታቸውን ገልፀዋል።

ታዋቂዎቹ ዓለምዓቀፍ ኩባንያዎች ቮዳኮም፣ ቮዳፎን፣ ሳፋሪኮም፣ ኢቲሳላት፣ አክሲያን፣ ኤምቲኤን እና ሌሎችም እንደሚገኙበትም ጠቅሰዋል።

ለሁለት አዳዲስ ቴሌኮም ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል የዋጋ ትመና ስራ ተጠናቆ በአማካሪዎች የተሰሩ የዋጋ ግመታ ስራዎችን በሶስተና ወገን የማስገምገም ሂደት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑም ተነግሯል።

በበጀት ዓመቱ ለሁለት አዳዲስ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት ከመንግስት የሚሰጥ አቅጣጫ በመቀበል ጨረታ የማውጣት ስራው በቀጣይ የሚከናወን መሆኑም እንዲሁ።

ዓለምዓቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት የራዲዮ ቴሌኮሙኒኬሽን ቢሮ 195 አባል አገራት ያሉት ሲሆን ኢትዮጵያም እ.አ.አ 1913 አባል ሆና መመዝገቧን መረጃዎች ያመላክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም