በሩብ ዓመቱ ከወጪ ንግድ 838 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል... ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

84

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2013(ኢዜአ)  በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከወጪ ንግድ 838 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር  አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ከተጠሪ ተቋሟት ጋር ዛሬ እየገመገመ ነው።

ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ድረገጹ ይፋ ባደረገው መረጃ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተለያዩ ምርቶች ወደውጭ ተልከው 838 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን አስታውቋል።

በተለያዩ ዘርፎች ወደ ውጭ ከተላኩት መካከል የማዕድን ዘርፉ የዕቅዱን 300 በመቶ በመላክ 205 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር አስገኝቷል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉ 95 በመቶ በመላክ 94 ሚሊዮን አሜሪካን ዶላር ያስገኘ ሲሆን በግብርና ውጤቶች ከዕቅዱ 73 በመቶ ተልኮ 541 የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማስገኘቱን  ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የወጪ ንግድ ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ115 ነጠብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም በ16 በመቶ መጨመሩም ተመላክቷል፡፡

የወጪ ምርቶች ውል ምዝገባና አፈጻጸም መመሪያ ለወጪ ንግዱ መሻሻል አይነተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉም  ተገልጿል።

በወጪ ምርቶች ንግድ ላይ የሚፈጸሙ ውሎችን ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው የውል ምዝገባ አፈፃፀም ስርዓት እንዲዘረጋ መደረጉ፣ ያለአግባብ የምርት ክምችት እንዳይኖ መደረጉ እንዲሁም የወጪ ምርቶች ግብይት ከዓለምአቀፍ  ገበያ ጋር ተነባቢ እንዲሆንና  የዋጋ መሻሻል መደረጉ ለወጪ ንግዱ መሻሻል  በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

"በሌላ በኩል በፌደራል እና በክልል መንግስታት መካከል ያለው ደካማ ቅንጅት እና ወጥነት የሌለው የግብይት ህጎች ትግበራ ለከፍተኛ ህገወጥ ግብይት በር መክፈቱ እንደ ድክመት ይጠቀሳል" ሲል ሚኒስቴሩ አስረድቷል።

ከፍተኛ የምርት መጠን በአቅራቢዎች መያዙ፣ የዓለምአቀፍ የምርቶች ዋጋ መቀነስ ና የመጀመሪያ የግብይት ማዕከላት በበቂ ሁኔታ አለመሟላት የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በድንበር አካባቢ ያለው የኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ የንግድ ቁጥጥር መላላት ከገጠሙ ችግሮች መካከል መሆኑም ተጠቅሷል።

እነዚህን ችግሮች በማስወገድ በቀጣይ የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ በቅንጅት እንደሚሰራ ተቋሙ በማህበራዊ ድረ ገጹ ባሰራጨው መረጃ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም