በደዌ ሀረዋ ወረዳ በተከሰተ የተሸከርካሪ አደጋ የሰዎች ህይወት አለፈ

49

ደሴ፣ ጥቅምት 16/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዌ ሀረዋ ወረዳ በተከሰተ የተሸከርካሪ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ19 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡


አደጋው የደረሰው ታርጋ ቁጥር  ኮድ 3-05220 አማ የሆነ የጭነት አይሱዙ ከእቃ በላይ ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ አሳፍሮ በመጓዝ ላይ እንዳለ በወረዳው  ቡራርሳ ቀበሌ ትናንት  በመገልበጡ ነው።

በዚህም  የሁለት ሰው ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ በ19 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በዞኑ  ፖሊስ መምሪያ የመረጃ ኦፊሰር ምክትል ሳጅን ኢብራሂም አራጌ ለኢዜአ አስታውቀዋል።

የተጎዱት ሰዎች በደሴ ሪፈራል ሆስፒታልና ከሚሴ ጤና ጣቢያ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ የሟቾቹ  አስክሬንም ለቤተሰቦች መላኩን ገልጸዋል።

አሽከርካሪው ለጊዜው ሸሽቶ ከአካባቢው ቢያመልጥም  በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ቢሆንም ከአደጋው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በፍጥነት ማሽከርከር ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ብለዋል ኦፊሰሩ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም