ወጣቶች በከፋፋዮች ሴራ ሳይታለሉ ለሀገራቸው ሰላምና አንድነት ዘብ መቆም አለባቸው--- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

75

አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2013 (ኢዜአ) ወጣቶች የኢትዮጵያን አንድነት በማይፈልጉ ከፋፋዮች ሴራ ሳይታለሉ ለሀገራቸው ሰላምና አንድነት ዘብ እንዲቆሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የሐይቅ - ቢስቲማ - ጭፍራ  የአስፋልት  ኮንክሪት  መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን ዛሬ በይፋ  ሲያስጀምሩ  ባስተላለፉት  መልዕክት ነው።

የመንገድ ግንባታው 74 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ያገናኛል።

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያም ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን  ብር በላይ ወጪ  መመደቡ  ነው  የተጠቆመው።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚህን ወቅት የፕሮጀክቱ መጀመር በአንበጣ መንጋ ለተጎዳው አካባቢ የኢኮኖሚ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄ የመለሰ መሆኑም አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው መንገዱ በአካባቢው ነዋሪዎች መካካል ጠንካራ የንግድ ልውውጥና ትስስር እንዲኖር በማስቻል ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ይህን በመረዳት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በመበጀት መንገዱን እንዲጀመር መወሰኑን ነው የገለጹት።

ፕሮጀክቱ በታቀደለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የአካባቢው ማህበረሰብ አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር እንዲያደርግም ዶክተር ዐቢይ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ የመንገድ ግንባታ ሥራውን በአራት ዓመት  ጊዜ ውስጥ  ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለታል።

"ጠላቶቻችን እኛን ማሸነፍና ያቀድነውን ልማት ማደናቀፍ የሚችሉት ስንከፋፋል ብቻ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፣ በተለይ ወጣቶች አብሮነታቸውን ጠብቀው ለሀገር ህልውና ዘብ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

"የኢትዮጵያን አንድነት ለማይፈልጉ ከፋፋዮች ዜማ ጀሮ አትስጡ" ሲሉም ነው የመከሩት።

የሐይቅ - ቢስቲማ - ጭፍራ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ  ግንበታ ፕሮጀክትን "ፓወርኮን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር" እና አሰር  ኮንስትራክሽን  በሽርክና እንደሚያከናውኑት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም