ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጣናን ከእንቦጭ ለመታደግ በሚደረገው ዘመቻ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ

112

አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2013 (ኢዜአ) “በኅብር ጣናን ከእንቦጭ እናድን” የሚለውን አገራዊ የንቅናቄ ዘመቻ በመቀበል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የድርሻውን እንዲወጣ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ጥሪ አቀረቡ።

የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች ጣናን ከእንቦጭ አረም ለመታደግ በሚደረገው ዘመቻ ተሳትፈዋል ። 

“በኅብር ጣናን ከእንቦጭ እናድን” የሚለውን አገራዊ የንቅናቄ ዘመቻ በመቀበል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የድርሻውን እንዲወጣ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ጥሪ አቅርበዋል። 

የትራንስፖርት ሚኒስቴር የ2013 ዓ .ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን በባህር ዳር ከተማ ገምግሟል።

ለሁለት ቀናት ተካሂዶ ዛሬ በተጠናቀቀው ግምገማ የተሳተፉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የተጠሪ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም የክልልና የከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች በእንቦጭ ማስወገድ ዘመቻ ላይ ተሳትፈዋል።

ለአንድ ወር በተላለፈው አገራዊ ጥሪ ላይ የተሳተፉት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ህዳሴ ግድብ ያለ ዓባይ ፤ ዓባይም ያለጣና የሚታሰቡ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

በመሆኑም የንቅናቄው ዘመቻ ግቡን እንዲመታ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንቦጭን በመከላከል ዘመቻ በመሳተፍ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

እስካሁን ድረስ በዘመቻው በቁርጠኝነት እየተሳተፉ ያሉ አርሶ አደሮች ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም የፌደራልና የክልል አመራር አካላትንም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም