ሩህሩህ፣ ተንከባካቢና አገልጋይ የጤና ባለሙያ ለመፍጠር ሚኒስቴሩ በትኩረት ይሰራባቸዋል

129

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 14/2013(ኢዜአ) ሩህሩህ፣ ተንከባካቢና አገልጋይ የጤና ባለሙያ መፍጠር የጤና ሚኒስቴሩ በዋናነት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ዋነኞቹ እንደሆኑ ተገለጸ።

የጤና ባለሙያዎች ካውንስል ለመመስረት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። 

ካውንስሉ የጤናውን ዘርፍ በእውቀትና ክህሎት ለመምራትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም ተጠቁሟል።


ላለፉት ስምንት ወራት ሲተገበር የቆየው ሩህሩህ፣ ተንከባካቢና አክባሪ የጤና ባለሙያዎች መርሃግብር የማጠቃለያ መርሃግብር ተከናውኗል።

መርሃግብሩ በጤና ሚኒስቴር መሪነትና በኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር አስተባባሪነት በሰባት የሙያ ማኅበራት ጥምረት ሲተገበር ቆይቷል።

አስተባባሪው አቶ ታምራት ሺህፈራው በጤና ባለሙያዎች፣ የጤና ትምህርት በሚሰጡ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ በሁለተኛ ደረጃና ቅድመ ኮሌጅ ተማሪዎችና የጤና ትምህርት ሲከታተሉ በቆዩ ተመራቂ ተማሪዎች ላይ አተኩሮ መሰራቱን ገልፀዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎች በሩህሩህ፣ ተንከባካቢና አክባሪ የጤና ባለሙያነት ዙሪያ ገለፃ ተደርጎላቸዋል፤ 208 መምህራንን አርአያ ለማድረግም ተሰርቷል።

በሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ያሉ 105 መምህራንና ከ600 በላይ ተማሪዎችም ስልጠና አግኝተዋል።

በትምህርት ቤቶች በተፈጠሩ ክበቦች ሩህሩህነትና ተንከባካቢነት በተግባር የተገለፁበት የበጎ ፍቃድ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልፀዋል።

የሙያ ማኅበራቱ ጥምረት ጥራት ያለው አገልግሎት የመስጠት የጋራ ግብን ያነገበና የእርስ በእርስ መማማሪያ መድረክ የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሰባት የሙያ ማኅበራት የተጀመረው ጥምረት ወደ11 ማደጉንና በቀጣይም 18 የሙያ ማኅበራትን አካቶ እንደሚሰራ አክለዋል።

ስልጠና ያገኙ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቶች ሕጎች ያፈነገጡና በሱስ የተጠመዱ ተማሪዎችን አርቀው መመለስ ያስቻለ መሆኑንም ነው አቶ ታምራት የገለፁት።

የተለያዩ ዶክመንተሪዎችን በመስራት የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ መሰራቱንም አክለዋል።

በመርሃግብሩ ማጠቃለያ በተካሄደ ውይይት አስተያየታቸውን የሰጡት የሙያ ማኅበራት ተወካዮች አቶ ሮቤል ተዘራና ዶክተር አለማየሁ ሐዲስ ባለፉት ስምንት ወራት የተሰራውን ስራ አድንቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂም ሩህሩህ፣ ተንከባካቢና አገልጋይ የጤና ባለሙያ መፍጠር ሚኒስቴሩ በዋናነት አትኩሮ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ዋነኛው እንደሆነ ተናግረዋል።

ተንከባካቢና ሩህሩህ የጤና ባለሙያ ከመፍጠር ባሻገር አሰራርን ተገልጋይን የሚያከብር ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ኀብረተሰቡ ወደ ጤና ተቋማት ሲመጣ ከጥበቃ ሠራተኛ ጀምሮ የሚያገኛቸው አገልግሎቶች ርህራሄን የተላበሱ መሆን እንዳለባቸውም አንስተዋል።

ሚኒስቴሩም አሰራሩን በዚህ መልኩ ለመቃኘት የሚሰራቸውን ስራዎች ያጠናክራል ብለዋል።

መርሃግብሩ በሁለተኛ ምዕራፍ እንደሚቀጥል ተገልፇል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም