በጉራፈርዳው ጥቃት እጃቸው ያለበት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

68

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት እጃቸው ያለበት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ያደረገው ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ልዑክ አስታወቀ።

በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በቅርቡ ማንነታቸው ባልታወቀ ቡድኖች በተፈጸመ ጥቃት የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ በርካታ ዜጎች መፈናቀላቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ያካተተ ቡድን በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ህዝባዊ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱም በቅርቡ በአካባቢው በተፈጸመ ጥቃት የተፈናቀሉ ዜጎችና ሌሎች የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ጥቃት የደረሰባቸው ተፈናቃዮች በዚህ ወቅት ጥቃቱ የተፈጸመው በአካባቢው ማህበረሰብ ሳይሆን የግል አጀንዳ ባለቸው ቡድኖች መሆኑን እንደሚያምኑ ነው ያስረዱት።

መንግስት እነዚህ የተደራጁ ህገ ወጥ ቡድኖች ላይ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።

በውይይቱ የተገኙ የሸኮ ማህበረሰብ ተወላጆችም ጥቃቱ አውግዘው፤ በአካባቢው ከሚኖሩ ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች ጋር ያላቸውን አብሮነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት።

በጥቃቱ እጃቸው ያለበት ግለሰቦችና የመንግሥት አመራሮች ላይ እርምጃ እንዲወሰድም የውይይቱ ተሳታፊዎች በጋራ ጠይቀዋል።

ልዑኩን የመሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ድርጊቱ በህዝቦች መካካል የተፈጸመ ግጭት ሳይሆን በጥቂት ህገ-ወጥ ቡድኖች የተከናወነ ጥቃት መሆኑን አብራርተዋል።

በድርጊቱ እጃቸው ያለበትን ህገ-ወጥ ቡድኖች ለህግ ከማቅረብ በተጨማሪም የአካባቢው አመራሮች ላይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም በጥቃቱ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ 21 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመጠቆም።

በተጨማሪ የአካባቢውን ሚሊሻ ፈትሾ እንደአዲስ በማዋቀር በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ይሰራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጀመረችው የለውጥ ጉዞ ያልተደሰቱ አካላት አሁንም ዜጎችን በማባላት ሀገር ለማፍረስ የተለያዩ ሙከራዎችን እንደሚያደርጉም ነው አፈ ጉባኤው የጠቆሙት።

ከዚህ አንጻር ዜጎች ሀገራቸውን ሰላም በመጠበቅ ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡም  ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው በበኩላቸው ለተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ወንጀለኞችን ለህግ ፊት የማቅረቡ ስራም እንዲሁ።

የጸጥታ መዋቅሩ የአካባቢውን በማረጋጋት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየሰራ መሆኑንም አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም