ሚኒስቴሩ ኮቪድ-19ን ለመከላከል በተደረገው አገራዊ ጥሪ የበኩላቸውን የተወጡ ወጣቶችን አመሰገነ

52

 አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር ኮቪድ-19ን ለመከላከል በተደረገው አገራዊ ጥሪ  የበኩላቸውን ለተወጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የምስጋና ምስክር ወረቀት ሰጠ። 

ባለፉት አራት ወራት ወረርሽኙን ለመከላከል በበጎ ፈቃድ ስራ ላይ ተሰማርተው ለሰጡት የነጻ አገልግሎት ምስጋናና እውቅና የተቸራቸው 34 ወጣቶች ናቸው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ድጉማ አገር በከፍተኛ ጭንቅ ላይ ባለችበት ወቅት ወጣቶቹ በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል ያሳዩት ቁርጠኝነት አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።

ወጣቶቹ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተመርቀው ስራ በማፈላለግ ላይ የነበሩ ሲሆኑ ኮቪድ-19 በተስፋፋበት ወቅት አገራቸውን ማገልገላቸውን ተናግረዋል።

ይህን ዓይነት በጎ ተግባር መለመድ እንዳለበት የገለጹት ዶክተር ደረጄ ወጣቶቹ አገሪቷ ኮቪድን ለመከላከል ባደረገችው ጥረት ትልቅ አቅም ሆነዋታል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ ስለ በሽታው እውቀት ኖሮት እንዲከላከል፣ የሕክምና መሳሪያዎችን በመጠገን፣ በሃብት ማሰባሰብና በሌሎችም ስራዎች እገዛ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የጤና ሚኒስቴር ብቻውን መወጣት ስለማይችል የበጎ ፈቃደኞች ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል።

ወጣቶቹ አገራቸውን ለማገልገል ያሳዩት ተነሳሽነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አርአያነታቸው እንዲስፋፋ መሰራት አለበትም ብለዋል።  

በበጎ ፋቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩት ሕሊና እምቢበልና እዮሲያስ ዘውዴ በሰጡት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አገራቸውንና ራሳቸውንም መጥቀም እንደቻሉ ነው የተናገሩት።

ያለስራ ሊያሳልፏቸው የነበሩትን አራት ወራት ኅብረተሰባቸውን ማገልገል በመቻላቸው የሕሊና እርካታ ማግኘታቸውንም ገልፀዋል።

ወጣቶቹ ልምዳቸውን ለሌሎች በማካፈል አገራዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በአገሪቷ እየሰፋፋ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የበጎ ፈቃድ ስራ የሚሰሩ ወጣቶችን እየመለመሉ መሆኑም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም